
ባሕር ዳር: ሕዳር 27/2018 ዓ.ም (አሚኮ) በማዕከላዊ ጎንደር ዞን በወገራ ወረዳና አካባቢው እራሱን ጎንደሬ በጋሻው እያለ የሚጠራው ቡድን አባል የነበሩ በርካታ ታጣቂዎች የመንግሥትን የሰላም ጥሪ ተቀብለዋል።
የማዕከላዊ ጎንደር ዞን ዋና አሥተዳዳሪ አወቀ አስፈሬ የሰላም አማራጩን ለተቀበሉ አካላት አቀባበል አድርገዋል።
በዚህም በዞኑ በተሳሳተ መንገድ ትጥቅ ይዘው ጫካ ገብተው የነበሩ በርካታ ታጣቂዎች የመንግስትን የሰላም ጥሪ ተቀብለው እየገቡ መሆኑን ገልጸዋል።
በዞኑ በተለያየ ጊዜ በርካታ ታጣቂዎች የመንግስትን የሰላም ጥሪ እየተቀበሉ መግባታቸውን ያስታወቁ ሲሆን በዛሬው እለትም ከ30 በላይ ታጣቂዎች ከእነ ትጥቃቸው የሰላም አማራጩን ተቀብለዋል ብለዋል።
ለታጣቂዎቹም የሰላም አማራጭን መርጣችሁ መምጣታችሁ ለሕዝባችሁ ያላችሁን ቁርጠኝነት የሚያረጋግጥ ነው ብለዋል።
የሰላም ጥሪውን ተቀብለው ለገቡት ታጣቂዎችም አስፈላጊው ድጋፍ እንደሚደረግላቸው አስታውቀዋል።
የአማራ ክልል ሰላምና ጸጥታ ቢሮ ምክትል ኃላፊ በሪሁን መንግሥቱ የክልሉን ሰላም ለማረጋገጥ መንግስት በተደጋጋሚ የሰላም አማራጭ እያቀረበ እንደሚገኝ ገልጸዋል።
በዚህም መሰረት በክልሉ የተለያዩ አካባቢዎች የመንግስትን የሰላም ጥሪ ተቀብለው እየመጡ ያሉ ታጣቂዎችን መቀበሉ እንዳለ ሆኖ ሕግ የማስከበሩ ስራ ተጠናክሮ ይቀጥላል ብለዋል።
የሰላም ጥሪውን ተቀበለው ለተመለሱ ታጣቂዎችም የተሃድሶ ስልጠና በመስጠት ወደ መደበኛ ሥራቸው እንዲመለሱና ተደራጅተው የሥራ እድል ተጠቃሚ እንዲሆኑ ይደረጋል ብለዋል።
የሰላም ጥሪ ከተቀበሉት መካከል ቻሌ ተዘራ በሰጠው አስተያየት በእኛ ምክንያት በሕዝባችን ላይ ዘረፋ፣ ግድያና ስርቆት እንዲበራከት ሆኗል ብሏል።
በመሆኑም በተለያየ ጊዜ የበደልነውን ሕዝብ ለመካስ ተዘጋጅተናል፤ የእርስበርስ መገዳደሉ ይብቃን ብሏል።
በዚህም ለተደረገላቸው የሰላም ጥሪ መንግስትን አመስግነው በቀጣይ ዘላቂ ሰላም እንዲረጋገጥ ከመንግሥት ጎን ተሰልፈው ለሰላም ዝግጁ መሆናቸውን አረጋግጠዋል።
በአቀባበል ፕሮግራሙ የክልል፣ የዞንና የወረዳ የሥራ ኃላፊዎች፣ የመከላከያ ሠራዊት አመራሮችን ጨምሮ የሚመለከታቸው አካላት ተገኝተዋል።
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
