
ባሕር ዳር፡ ኅዳር 27/2018 ዓ.ም (አሚኮ) የአማራ ክልል የሥነ ምግባር እና ጸረ ሙስና ኮሚሽን ”ትውልድን በሥነ ምግባር፤ ተቋምን በአሠራር” በሚል መሪ መልዕክት ሲያከብር የቆየውን 22ኛውን ዓለም አቀፍ የጸረ ሙስና ቀን የማጠቃለያ መድረክ አካሂዷል።
በመድረኩ የክልሉ ሲቪል ሰርቪስ እና የሰው ሃብት ልማት ኮሚሽን ኮሚሽነር ባንቻምላክ ገብረማርያምን ጨምሮ ሌሎች የክልሉ ባለሥልጣናት ተገኝተዋል፡፡
የሞሰብ አንድ ማዕከል አገልግሎት ሠራተኞች ጋርም ስለ ትውልድ ሥነ ምግባር ቀረጻ፣ የአገልግሎት አሰጣጥ ቅልጥፍና፣ ግልጸኝነት እና ተጠያቂነት እንዲሁም ሕዝብን በአገልግሎት አሰጣጥ ስለማርካት ውይይት ተደርጓል፡፡
የውይይቱ ተሳታፊ በአማራ ክልል ሞሰብ የአንድ ማዕከል አገልግሎ አሥተባባሪ ተማረ አቤ ትውልድ በሥነ ምግባር ካልታነጸ አገልግሎት አሰጣጥን ማሳለጥ እንደማይቻል አንስተዋል፡፡ የተቋምን አገልግሎት በአሠራር ማሳለጥ ከሞሰብ የአንድ ማዕከል አገልግሎት ጋር እንደሚቆራኝ ገልጸዋል፡፡
ሞሰብ የአንድ ማዕከል አገልግሎት በየተቋሙ የሚታዩ የአገልግሎት አሰጣጥ ችግሮችን ለመቅረፍ መቋቋሙን ገልጸዋል፡፡ በ14 የክልል እና የፌዴራል ተቋማት 54 አገልግሎቶች እየተሰጡበት መኾኑንም ተናግረዋል፡፡ በሂደትም እያደገ እንደሚሄድ ጠቁመዋል፡፡
በማዕከሉ የሚሰጡ አገልግሎቶች ለነገ የማይባሉ እና በፍትሐዊነት የሚሰጡ በመኾኑ ተገልጋዮች ደስተኛ መኾናቸውን አንስተዋል፡፡
በሞሰብ የአንድ ማዕከል አገልግሎት የበጎ ፈቃድ አገልግሎት የምትሰጠው ወጣት ሮዛ ጌታቸው በበኩሏ የአንድ ሞሰብ አገልግሎት ብልሹ አሠራርን ለመቅረፍ መቋቋሙን ጠቅሳ የተገልጋይን እርካታ ምዘና እንደምትሠራ ተናግራለች፡፡ ውጤቱም መልካም መኾኑን ነው የገለጸችው፡፡
ብልሹ አሠራርን ለማጥፋት የአንድ ሞሰብ ማዕከል አገልግሎት ብቻውን በቂ አይደለም፤ ሌሎች ተቋማት እና የሚመለከታቸው አካላት ኀላፊነታቸውን መወጣት ይገባቸዋል ነው ያለችው፡፡
የአማራ ክልል ሥነ ምግባር እና ጸረ ሙስና ኮሚሽን ኮሚሽነር ሀብታሙ ሞገስ በኢትዮጵያ ለ21ኛ ጊዜ የጸረ ሙስና ቀን ሲከበር የሙስና ችግሮችን ለመፍታት የችግሩን አስከፊነት ለኅብረተሰቡ ለማስገንዘብ እንደኾነ አንስተዋል፡፡
ሀገርን የሚረከብ ትውልድ ለመፍጠር እና ብልጽግናን ለማረጋገጥ በሥነ ምግባር የታነጸ ትውልድ አስፈላጊ እንደኾነ አንስተዋል፡፡ በየደረጃው የትውልድ ሥነ ምግባርን ለመገንባት እና ሙስናን ለመታገል የተለያዩ ተቋማዊ ሪፎርሞች መደረጋቸውንም አንስተዋል፡፡
በአማራ ክልልም የአንድ ማዕከል ሞሰብ አገልግሎት በከተሞች መጀመሩን እና የተቀላጠፈ አገልግሎት እየሰጠ መኾኑን ገልጸዋል፡፡ በሂደትም ሁሉም ተቋም አሠራሩን ወስዶ አገልግሎት አሰጣጡን ዲጂታላይዝድ ማድረግ እንደሚጠበቅበት አንስተዋል፡፡
ኮሚሽነር ሀብታሙ ለትውልድ ግንባታም ኾነ ብልሹ አሠራርን ለመታገል ባለድርሻ አካላት ሚናቸውን እንዲወጡም ጥሪ አስተላልፈዋል፡፡
የአማራ ክልል ሲቪል ሰርቪስ እና የሰው ሃብት ልማት ኮሚሽን ኮሚሽነር ባንቻምላክ ገብረማርያም ተቋማትን በመገንባት የአገልግሎ አሰጣጥን በማሳደግ የኅብረተሰብን እርካታ ከፍ ማድረግ ይገባል ብለዋል። ለዚህም የመንግሥት አገልግሎት እና አሥተዳደር ማሸሻያ አካል የኾው ሞሰብ የአንድ ማዕከል አገልግሎት ተጠቃሽ እንደኾነ አንስተዋል፡፡
በማዕከሉ ተገልጋይ የሚበዛባቸውን አገልግሎቶችን በመለየት፣ ዲጂታላይዝድ በማድረግ፣ ወደ አንድ ማዕከል በማምጣት እና ብቃት ባለው የሰው ኀይል በመፈጸም አገልግሎ እየተሰጠ መኾኑን ገልጸዋል፡፡
አገልግሎቱን በባሕር ዳር፣ ጎንደር እና ደሴ ለመተግበር ሥራዎች እየተሠሩ እንደኾነም አብራርተዋል፡፡ አገልግሎቱን በሌሎች ከተሞችም ለማስፋት ጥረት እየተደረገ መኾኑንም ጠቁመዋል፡፡ በአንድ ከተማ አንድ የሞሰብ ማዕከልን የመፍጠር ተነሳሽነትን ለመተግበር በ24 ከተሞች ተግባራዊ ለማድረግ አቅጣጫ መሰጠቱንም ገልጸዋል፡፡
በአገልግሎት አሰጣጡ የሕዝብ እርካታ እየተፈጠረ መኾኑን የጠቀሱት ወይዘሮ ባንቻምላክ የተቋም ግንባታ ሥራ በአሠራር እየተጠናከረ እንደሚሄድም አብራርተዋል፡፡
በሥነ ምግባር የታነጸ ትውልድ ለመፍጠር የሚደረገው እንቅስቃሴም በአገልግሎት መስጫ ማዕከሉ የሚገቡ ሠራተኞችን ሥነ ምግባር የተሻለ እንዲኾን ማድረግ ያስችላልም ነው ያሉት፡፡
ተቋም መገንባት ቁሳቁስ ማሟላት ሳይኾን በተሰማሩበት የሥራ መስክ ሕዝብን ማገልገል እና ውጤታማ መኾን ነው ያሉት ኮሚሽነሯ ኅብረተሰብን ማገልገል ለነጋችን እርሾ ማስቀመጥ በመኾኑ በቅንነት እንደሚያገለግሎም አስገንዝበዋል፡፡
ዘጋቢ፦ ዋሴ ባዬ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
