
ደሴ፡ ኅዳር 27/2018 ዓ.ም (አሚኮ) የአማራ ክልል ንግድ እና ገበያ ልማት ቢሮ ሕገ ወጥ የንግድ እንቅስቃሴን በመቆጣጠር የዋጋ ንረትን ለመቀነስ ከ45 ወረዳዎች እና ከከተማ አሥተዳደሮች ለተውጣጡ የንግድ ባለሙያዎች በኮምቦልቻ ከተማ ሥልጠና እየሰጠ ነው።
የአማራ ክልል ንግድ እና ገበያ ልማት ቢሮ ኀላፊ ኢብራሂም ሙሃመድ (ዶ.ር) በክልሉ የኑሮ ውድነትን ለመቀነስ አምራች እና ሸማች በቀጥታ የሚያገናኙባቸው የገበያ አማራጮች መመቻቸቱን ተናግረዋል።
አንደኛ እና ሁለተኛ ደረጃ የግብይት ማዕከላትን ሥራ ከማስጀመር ባሻገር ከእሑድ እስከ እሑድ የሚከናወን የገበያ ማዕከል ሸማቾችን ተጠቃሚ ማድረጉን አንስተዋል።
የዋጋ ጭማሪ እንዲፈጠር ምክንያት የኾኑ አሠራሮችን ለማስተካከል እየተሠራ እንደኾነ የገለጹት ኀላፊው የኬላ ላይ ቀረጥ ሙሉ በሙሉ እንዲነሳ አቅጣጫ መሰጠቱንም አመላክተዋል።
በቀጣይም ሕገወጥነትን በመከላከል እና አምራቹን በቀጥታ ከሸማቹ ጋር በማገናኘት ውጤታማ ሥራ ለማከናወን እንደሚሠራም ገልጸዋል።
እየተሰጠ ያለው ሥልጠናም የዘርፉ ባለሙያዎች ግንዛቤ አግኝተው ሥራቸውን በውጤታማነት እንዲያከናውኑ ለማድረግ እንደሚያግዝ ተናግረዋል።
ከአሚኮ ጋር ቆይታ ያደረጉ በደሴ ከተማ ንግድ እና ገበያ ልማት መምሪያ የገበያ መሠረተ ልማት ባለሙያ አሕመድ ይመር እና በሲያደብርና ዋዩ ወረዳ የንግድ ጽሕፈት ቤት የግብይት ቡድን መሪ ሲሳይ አጥናፉ በመንግሥት በኩል የብድር አቅርቦት በማመቻቸት የዋጋ ንረቱን ለመቀነስ እየተሠራ ነው ብለዋል።
በዚህም የግብርና እና የኢንዱስትሪ ምርቶችን በተመጣጣኝ ዋጋ ለሸማቹ ለማድረስ እየተሠራ መኾኑንም አንስተዋል።
ባለሙያዎቹ ከሥልጠናው ጎን ለጎን በኮምቦልቻ ከተማ የተገነቡ የግብይት ማዕከላትን የተመለከቱ ሲኾን በቀጣይ የንግድ ሥራውን ውጤታማ ለማድረግ ይበልጥ እንደሚሠሩ ገልጸዋል።
ዘጋቢ:- ተመስገን አሰፋ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
