
ጎንደር፡ ኅዳር 27/2018 ዓ.ም (አሚኮ) የጎንደር ከተማ አሥተዳደር ከማዕከላዊ ጎንደር ዞን እና ከከተማ አሥተዳደሩ ከተውጣጡ የጸጥታ አካላት ጋር ውይይት አካሂዷል። በውይይቱ ሰላምን ለማረጋገጥ የሚተጉ ሌሎች አጋር አካላትም ተገኝተዋል።
ውይይቱ ዘላቂ ሰላምን ለማረጋገጥ ያለመ ሲኾን በከተማዋ እየተሠራ ያለው የቁጥጥር እና ሰላምን የማስፈን ተግባር አበረታች መኾኑ ተነስቷል።
በከተማው እየተተገበሩ የሚገኙ የምሽት ቁጥጥር ሥራዎች፣ የኮሚኒቲ ፖሊሲንግ ማቋቋም ተግባራት እና የብሎክ አደረጃጀቶችን ተግባራዊ ያደረጉ ሥራዎች እየተከናወኑ መኾኑን የውይይቱ ተሳታፊዎች አንስተዋል።
የከተማዋን ሰላም ዘላቂ ለማድረግ በዋናነት ሕገ ወጥ የሰዎች እና የጦር መሳሪያ ዝውውር እንዲሁም ሕገ ወጥ ተሽከርካሪዎችን መከላከል ላይ ትኩረት ተሰጥቶ የሚሠራባቸው ተግባራት መኾናቸውንም የጸጥታ አካላቱ ተናግረዋል።
የጎንደር ከተማ አሥተዳደር ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ ቻላቸው ዳኘው ሕገ ወጥ ተሽከርካሪዎችን ለመከላከል የትራንስፖርት ሥርዓቱን ማዘመን ላይ እየተሠራ መኾኑን አስረድተዋል።
የጸጥታ መዋቅሩ የምሽት ጥበቃ ሥራውን አጠናክሮ እንዲቀጥል እየተሠራ እንደኾነም ጠቁመዋል። ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባው ከሕዳር 29/2018 ዓም ጀምሮ ባለ ሦሥት እግር ተሽከርካሪዎች የ24 ሰዓት አገልግሎት እንዲሰጡ ተፈቅዷልም ብለዋል።
የአማራ ክልል ሰላም እና ጸጥታ ቢሮ ምክትል ኀላፊ በሪሁን መንግሥቱ የጸጥታ መዋቅሩ ውድ ሕይዎቱን እየከፈለ በሠራው ተግባር አሁን አንጻራዊ ሰላም መገኘቱን አብራርተዋል።
አሁንም ያለውን የጸጥታ ችግር በዘላቂነት ለመፍታት ተግቶ መሥራት እንደሚጠይቅ ተናግረዋል።
ቢሮው የአድማ መከላከልን የመገንባት ተግባር በሠራው ሥራ መልካም ውጤት እንዳለ አንስተዋል።
ክልሉ የገጠመውን የጸጥታ ችግር በሚፈለገው ልክ በመገንዘብ ረገድ ክፍተቶች እንዳሉ ያነሱት አቶ በሪሁን ሕገ ወጥነትን በጋራ መከላከል ያስፈልጋልም ብለዋል።
ሕገ ወጥ የሰዎች ዝውውር እና በወንጀል ተግባር የተሳተፉ ግለሰቦችን ተጠያቂ የማድረግ ተግባርን ባሕል ማድረግ እንደሚያስፈልግም ተናግረዋል።
የሰላም አማራጭን በሚገፉ አካላት ላይ ጠንካራ ሕግ የማስከበር ሥራዎች እየተሠሩ መኾኑን የተናገሩት ደግሞ የአማራ ክልል ብልጽግና ፓርቲ ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት የፖለቲካ እና አቅም ግንባታ ዘርፍ ኀላፊ ዘሪሁን ፍቅሩ (ዶ.ር) ናቸው።
ለአማራ ሕዝብ ከማይጠቅሙ ተግባራት መቆጠብ ያስፈልጋል ያሉት ኀላፊው ኀብረተሰቡን እረፍት የሚነሱ አካላትን ማረም ይጠይቃል ብለዋል።
ለሰላም ዝግጁ የኾነ ማኅበረሰብ መፍጠር እንደሚያስፈልግም አንስተዋል።
በቅርቡ የሚከበረውን የጥምቀት በዓል ለማክበር ለሚመጡ እንግዶች የተመቸች ጎንደር ለመፍጠር እየተሠራ ባለው ተግባር የጸጥታ መዋቅሩ ጠንክሮ እንዲሠራም አሳስበዋል።
ዘጋቢ፦ አዲስ ዓለማየሁ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
