
ደብረ ብርሃን፡ ኅዳር 27/2018 ዓ.ም (አሚኮ) የ2018 ዓ.ም ዓለም አቀፍ የአካል ጉዳተኞች ቀን በዓለም እቀፍ ደረጃ ለ34ኛ ጊዜ፣ በኢትዮጵያ ደግሞ ለ33ኛ ጊዜ “አካል ጉዳተኝነትን የሚያካትት ማኅበረሰብ መገንባት ለተሻለ ማኅበራዊ እድገት” በሚል መሪ መልዕክት በክልል ደረጃ በደብረ ብርሃን ከተማ ተከብሯል።
በበዓሉ ላይ የተገኙት በምክትል ርእሰ መሥተዳድር ማዕረግ የገጠር ዘርፍ አስተባባሪ ድረስ ሳህሉ (ዶ.ር) አካል ጉዳተኝነት ከማኅበረሰቡ ጋር ተቀላቅሎ ለመኖር እና ለመሥራት የማያግድ መኾኑን የተረዳ ማኅበረሰብ መገንባት ያስፈልጋል ብለዋል።
በኢኮኖሚ፣ በማኅበራዊ እና በፖለቲካዊ ዘርፎች ላይ አካል ጉዳተኞች በሚጠበቀው ልክ ተጠቃሚ ባለመኾናቸው በይበልጥ አመለካከት መገንባት ላይ በትኩረት መሥራት ይገባል ብለዋል።
አካል ጉዳተኞች ለሀገር ግንባታ ያላቸው አበርክቶ ከፍተኛ መኾኑን መረዳት ይገባልም ነው ያሉት።
የአማራ ክልል ሴቶች፣ ወጣቶች እና ማኅበራዊ ጉዳይ ቢሮ ምክትል ኀላፊ ንጹህ ሽፈራው የአካል ጉዳተኞች ተሳትፎ ውስንነትን በማስተካከል የጋራ ተጠቃሚነትን ማጉላት እንደሚያስፈልግ አስገንዝበዋል።
አካል ጉዳተኞች ለሀገር ብልጽግና ያላቸው አስተዋጽኦ ከፍተኛ መኾኑን በመረዳት የአመለካከት ችግርን መቅረፍ፣ መሠረተ ልማቶችን ምቹ ማድረግ፣ ለተለያዩ ችግሮች እንዳይጋለጡ ማድረግ ይገባልም ብለዋል።
የደብረ ብርሃን ከተማ አሥተዳደር ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ በድሉ ውብሸት በኢኮኖሚ፣ በማኅበራዊ እና በሌሎችም ዘርፎች አካል ጉዳተኞችን አካቶ በመሥራት ተጠቃሚነታቸውን ለማጎልበት እየተሠራ እንደኾነም አስረድተዋል።
በማኅበራዊ ልማት ዘርፎች ላይ አካል ጉዳተኞች ተጠቃሚ እንዲኾኑ እየተሠሩ የሚገኙ ሥራዎች ተጠናክረው እንደሚቀጥሉም ነው የጠቆሙት።
አጋር አካላት ወደ ሥራ እንዲገቡ ለማድረግ በርካታ ሥራዎች እየተሠሩ መኾኑን አንስተው አካል ጉዳተኞችን ያካተተ ማኅበረሰብ ለመፍጠር እንደሚሠራም ተናግረዋል።
የደብረ ብርሃን ከተማ አሥተዳደር ሴቶች፣ ወጣቶች እና ማኅበራዊ ጉዳይ መምሪያ ኀላፊ በለጥሽ ግርማ በከተማ ደረጃ በየዘርፉ በስምንት ማኅበር የተደራጁ የተለያዩ አካል ጉዳተኞች መኖራቸውን ጠቁመው በከተማው ባሉ ኢንዱስትሪዎች እና በተለያዩ ተቋማት ተቀጥረው እንዲሠሩ እየተደረገ መኾኑን አንስተዋል።
አካል ጉዳተኞችን ተጠቃሚ ለማድረግም የሚሠሩ ሥራዎች ተጠናክረው እንደሚቀጥሉም ገልጸዋል፡፡
የአካል ጉዳተኞች ቀን መከበሩ ልዩ ትርጉም ያለው መኾኑን የተናገሩት የአማራ ክልል አካል ጉዳተኞች ማኅበራት ፌዴሬሽን ፕሬዝዳንት ፍሬስብሐት ዘገየ በዓሉ መከበር ከጀመረበት ጊዜ አንስቶ የተለያዩ ሕጎችን በማውጣት አካል ጉዳተኞች ተጠቃሚ እንዲኾኑ እየተሠራ መኾኑን አስረድተዋል።
በክልሉ 4ሚሊዮን አካል ጉዳተኞች መኖራቸውን ያነሱት ፕሬዝዳንቱ ከበዓል ማክበር ባለፈ አካታችነትን በተጨባጭ መሥራት ይገባል ነው ያሉት።
በማኅበራዊ፣ በፖለቲካዊ እና በኢኮኖሚው ዘርፍ አካል ጉዳተኞችን በማካተት ውጤታማ ሥራዎችን መሥራት እንደሚገባም ጠቁመዋል። አካል ጉዳተኞችን ያላካተቱ የልማት ሥራዎች መኖር የለባቸውም ብለዋል።
በበዓሉ አከባበር ላይ የተገኙ አካል ጉዳተኞች የበዓሉ መከበር ለማኅበረሰቡ የግንዛቤ ፈጠራ ሥራ የሚረዳ መኾኑን አንስተዋል።
አካል ጉዳተኞችን ተጠቃሚ ለማድረግ የወጡ ሕጎችን በአግባቡ መፈጸም ያስፈልጋልም ብለዋል። በቀጣይ ለአካል ጉዳተኞች የተመቼ አካባቢን መፍጠር እንደሚገባም ጠቁመዋል።
ዘጋቢ፦ ስንታየሁ ኃይሉ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
