
አዲስ አበባ: ኅዳር 27/2018 ዓ.ም (አሚኮ) በአምባሳደር ጄኔራል ባጫ ደበሌ የተጻፈው “የጸረ ሽምቅ ውጊያ ጥበብ” መጽሐፍ በይፋ ተመርቋል።
40 ዓመታትን በውትድርና ሕይዎት ውስጥ ያገለገሉት አምባሳደር ጄኔራል ባጫ ደበሌ ውትድርና ሕይዎት ነው፤ ለሀገር መሰዋት ክብር ነው፤ ከሁሉም ነገር በላይ ሀገርን መውደድ ቀዳሚ ነው ብለዋል። ሁላችንም ለኢትዮጵያ እናስፈልጋታለን፤ ኢትዮጵያ ወደር የሌላት፣ ብርቅዬ ሃብት እና ጌጣችን ናት ነው ያሉት።
ሁላችንም ያለንን ነገር እና ባለን አቅም፣ እውቀት እና ጥበብ ለሀገር እንዲጠቅም በሚረዳ መልኩ አዘጋጅተን መሥራት ማገልገል እና ማበርከት ይኖርብናል ብለዋል።
ኢትዮጵያ ታላቅ ሃብት እና ታሪክ ያላት ሀገር ናት ያሉት አምባሳደር ጄኔራል ባጫ ደበሌ “ባለን ጸጋ እንዳንጠቀም እንቅፋት በዝቷል”፤ ይህንን የምናሸንፈው በጋራ ቆመን ጠላቶቻችንን መመከት ስንችል ነው ብለዋል።
በሽምቅ ውጊያ ኢትዮጵያን ለማሸማቀቅ የሚፈልጉ ጽንፈኛ ኃይሎች የኢትዮጵያን የኋላ ታሪክ ያላወቁ የሕዝቦቿንም ባሕል፣ ታሪክ መከባበር እና ጀግንነት ያልተረዱ በመኾናቸው በጋራ ለውጥ እና በሠለጠነ አካሄድ ችግርን በጠረጴዛ ዙሪያ ለመፍታት መዘጋጀትን መልመድም አለባቸው ነው ያሉት።
ኢትዮጵያ በአፍሪካ ሀገራት በሁሉም መስክ ተመራጭ የኾነች ሀገር መኾኗን የገለጹት አምባሳደር ጄኔራል ባጫ ደበሌ ለጋራ ሰላሟ እና እድገቷ ሁላችንም መረባረብ አለብን ብለዋል።
በመጽሐፍ ምረቃ መርሐ ግብሩ ላይ የተገኙት የኢፌዴሪ ጦር ኃይሎች ኢታማጆር ሹም ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ በቀደመው ታሪካችን ውስጥ የተደረጉ እና እየተደረጉ ያሉ የሽምቅ ውጊያዎች ጸረ ኢትዮጵያ ውጊያ መኾናቸውን ተናግረዋል።
ትውልዱ ካለፈው ስህተት ተምሮ ለሀገር እድገት የሚበጁ አንድነትን የሚያመጡ ጉዳዮች ላይ በማተኮር የሀገርን ዳር ድንበር በጋራ በማስከበር እጅ ለእጅ ተያይዘን ሀገራችንን የበለጠ ከፍ ለማድረግ መሥራት አለብን ነው ያሉት።
የጸረ ሽምቅ ውጊያ ጥበብ መጽሐፍ ኢትዮጵያ እየገነባችው ላለው ዘመናዊ የመከላከያ ሠራዊት ግንባታ ትልቅ አቅም የሚፈጥር፤ ዘመኑን የዋጀ እና የሠለጠ አቀራረብ መኾኑን ነው የገለጹት። ይህ ከፍ ያለ ሥራ ጥሩ ምሳሌ ኾኖን ሌሎችም ከፍተኛ የጦር መኮንኖች የጄኔራል ባጫ ደበሌን ተሞክሮ እንዲወስዱ መልዕክት አስተላልፈዋል።
በአምባሳደር ጄኔራል ባጫ ደበሌ የተጻፈው “የጸረ ሽምቅ ውጊያ ጥበብ” መጽሐፍ ምረቃ መርሐ ግብር ላይ የጦር ኃይሎች ምክትል ኢታማጆር ሹም ጄኔራል አበባው ታደሰ፣ የብሔራዊ መረጃ እና ደኅንነት ዋና ዳይሬክተር አምባሳደር ሬድዋን ሁሴን፣ የቀድሞው የኢፌዴሪ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈ ጉባኤ አባዱላ ገመዳ፣ ከፍተኛ የጦር መኮንኖች፣ የፌዴራል እና የክልል ከፍተኛ የሥራ ኀላፊዎች በመድረኩ ታድመዋል።
ዘጋቢ:- ሰለሞን አሰፌ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
