
ባሕር ዳር፡ ሰኔ 14/2012 ዓ.ም (አብመድ) ኢትዮጵያ በታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ድርድር ሰበብ በዓባይ ወንዝ ላይ የሚኖራትን ቀጣይ የመልማት መብት የሚገድብ ስምምነት እንደማትቀበል የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ገዱ አንዳርጋቸው አረጋግጠዋል።
ኢትዮጵያ፣ ግብፅና ሱዳን በግድቡ የውሃ አሞላል ባደረጉት ድርድር በቴክኒካዊ ጉዳዮች ላይ ወደ ስምምነት ቢቃረቡም ሕግ ነክ በሆኑ ጉዳዮች የሚያቀራርቡ ሐሳቦች ተቋርጠዋል። ኢትዮጵያ በአሁኑ ወቅት የምታደርገው ድርድር ግድቡን በሚመለከቱ ጉዳዮች እንጂ በቀጣይ የዓባይን ወንዝ ተጠቅማ የመልማት መብቷን እንደማያካትት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ አቶ ገዱ ተናግረዋል።
ግብፅ በግድቡ ላይ የሚደረገውን ድርድር በማስታከክ ኢትዮጵያ በግድቡ ላይ የሚኖራትን መብት ለመገደብ እየሞከረች መሆኗንም አስረድተዋል። የግድቡ ጉዳይ የዓባይ ወንዝ ፍትሃዊ ተጠቃሚነት አንድ ነጠላ አካል ነው ያሉት ሚኒስትሩ የዓባይ ወይም የናይል ወንዝ ተጠቃሚነት መታየት ያለበት ሁሉም የተፋሰሱ አገሮች በተደራደሩበት የትብብር ስምምነት መሠረት መሆኑን አስረድተዋል።
ስምምነቱ የወንዙን ፍትሃዊ ተጠቃሚነትና ዓለም አቀፍ ስምምነቶችንም ማዕከል ማድረጉንና ግብፅ ከአሁኑ የሦስትዮሽ ድርድር አፈንግጣ መውጣቷንም ገልጸዋል።
ስምምነቱን ከተደራደሩት 10 አገሮች ስድስቱ መፈረማቸው ይታዎሳል፤ ከእነዚህም ኢትየጵያን ጨምሮ አራት አገሮች ስምምነቱን በፓርላማቸው አፅድቀው የሕጋቸው አካል አድርገውታል። በመሆኑም ኢትዮጵያ የዓባይን ወንዝ ተጠቃሚነት በተመለከተው ስምምነት መሠረት ወንዙን በፍትሃዊነት መጠቀም ትችላለች ብለዋል ሚኒስትሩ።
ሦስቱ አገሮች የሚያደርጉት ድርድር ግድቡን ብቻ እንደሚመለከትና ይህም ኢትዮጵያ በቀጣይ ሌላ ግድብ የመገንባትም ይሁን ፍትሃዊ በሆነ መንገድ ወንዙ የመጠቀም መብቷን የሚያስጠብቅ መሆን እንዳለበት አመልክተዋል።
ኢትዮጵያን ምንም ዓይነት ውጫዊም ይሁን ውስጣዊ ችግር ግድቡን ውሃ ከመሙላት እንደማያግዳት አቶ ገዱ መናገራቸውንም ኢዜአ ዘግቧል።
የታላቁ ኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ግንባታ 74 ከመቶ መድረሱና የውሃ ሙሌቱም በቀጣዩ ወር እንደሚጀመር መረጃዎች ያመለክታሉ።
