
ወልድያ: ኅዳር 27/2018 ዓ.ም (አሚኮ) የወልድያ ከተማ አሥተዳደር ገቢዎች መምሪያ” ተቋማዊ ፍቅር እና የአገልጋይነት መንፈስን መፍጠር ትልቅ ጸጋ ነው” በሚል መሪ መልዕክት በአዲሱ የታክስ አሥተዳደር አዋጅ ላይ ለመምሪያ እና ለክፍለ ከተማ የገቢ ባለሙያዎች ሥልጠና እየሰጠ ነው።
የከተማ አሥተዳደሩ ገቢዎች መምሪያ ኀላፊ ሞገስ አስማማው በ2018 በጀት ዓመት 1 ነጥብ 1 ቢሊዮን ብር ለመሰብሰብ ታቅዶ ተግባራት እየተከናወኑ ነው ብለዋል።
ይህን ዕቅድ ከግብ ለማድረስ የባለሙያውን አቅም ማጎልበት እና አዳዲስ አዋጆች ላይ ግንዛቤ መፍጠር አስፈላጊ መኾኑን ነው ያስረዱት።
ይህን ግምት ውስጥ በማስገባትም አዲሱ የታክስ አሥተዳደር አዋጅ 1395/2017 ላይ የከተማ አሥተዳደሩ የገቢዎች ባለሙያዎች ወጥ አረዳድ እንዲኖራቸው እየተሠራ ነው ብለዋል።
የአማራ ክልል ገቢዎች ቢሮ የግብር ትምህርት እና ኮሙዩኒኬሽን ዋና ዳይሬክተር ታዘባቸው ጣሴ ከግብር አዋጁ ባሻገር የሠራተኞችን የአገለጋይነት መንፈስ ማነቃቃት አስፈላጊ ነው ብለዋል።
የተቋም ፍቅር ከሌለ አገልጋይነት አይኖርም፤ “በሠራተኞች ውስጥ የተቋም ፍቅር ስር ከሰደደ ሠራተኛው ከልቡ ይሠራል ነው” ያሉት።
የሠራተኞችን እና የሥራ ኀላፊዎችን ፍቅር በማጠናከር መተሳሰብ እና መተማመን ላይ የተመሠረተ ግንኙነት መፍጠር እንደሚገባም አሳስበዋል።
አዲሱ የግብር አዋጅ ዝቅተኛ የግብር አከፋፈል ላይ አዲስ የተቀጣሪ ሠራተኞች የሥራ ግብር፣ የደረጃ ለ እና ደረጃ ሀ ግብር ከፋዮች የ2017 ዓ.ም የከፈሉትን ግብር በዚህ በጀት ዓመት በየሩብ ዓመቱ እንዲከፍሉ የሚያደርግ አሥተዳደር እና ሌሎች ማሻሻያዎች እንዳሉት ተመላክቷል።
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
