የሀገር ሽማግሌዎች እና የሃይማኖት አባቶች ለሰላም እየከፈሉት ያለው ዋጋ የሚደነቅ ነው።

7

ሰቆጣ: ኅዳር 27/2018 ዓ.ም (አሚኮ) ለአንዲት ሀገር ሁለንተናዊ እድገት ውስጣዊ እና ውጫዊ ሰላም የተረጋጋ መኾን መሠረታዊ ነገር ነው።

በአማራ ክልል ባለፉት ሦስት ዓመታት ያጋጠመውን የሰላም እጦት ለመፍታት ከመንግሥት ተደጋጋሚ የሰላም ጥሪ ባሻገር በሀገር ሽማግሌዎች እና በሃይማኖት አባቶች ዘንድ ሰላምን ለማምጣት በርካታ ተግባራት ተከናውነዋል።

በዋግ ኽምራ ብሔረሰብ አሥተዳደር ያለውን ሰላም ለማጽናት የሀገር ሽማግሌዎች ከአጎራባች ወረዳዎች ጋር በመነጋገር የተረጋጋ ሰላም እንዲኖር ማድረግ እንደቻሉ የስሃላ ሰየምት ወረዳ ሀገር ሽማግሌዎች ተናግረዋል።

አቶ ዓለማየሁ ደሴ የስሃላ ሰየምት ወረዳ የሀገር ሽማግሌ ሲኾኑ ግጭቶችን በማስታረቅ ይታወቃሉ። የእርስ በርስ ጦርነት ለሀገር የማይበጅ በመኾኑ ሁሉም ለሰላም ቅድሚያ ቢሠጥ መሠረታዊ ነገር ነው ባይ ናቸው።

ከአጎራባች ወረዳ የሀገር ሽማግሌዎች ጋር በመነጋገር ነጋዴው እንዲነግድ እና ሕዝብ ለሕዝብ እንዲገናኝ ለማድረግ በተደጋጋሚ መምከራቸውንም ነው የገለጹት። በዚህም ለውጥ መጥቷል ብለዋል።

ለሁሉም ነገር መሠረቱ ሰላም በመኾኑ የታጠቁ ኃይሎች ችግሮች በውይይት ለመፍታት የጀመሩትን ሥራ እንዲያጠናክሩም ጠይቀዋል።

ሰላምን ለማጽናት እናቶችም ልጆቻቸውን ሊመክሩ ይገባል ያሉት ደግሞ የምክር ቤት አባል ወይዘሮ ሙሉነሽ መኮነን ናቸው። “ከጦርነት የሚገኝ ጥቅም እና የሚመጣ ልማት ባለመኖሩ” ሰላማችንን መጠበቅ ይገባናል ብለዋል።

በስሃላ ሰየምት ወረዳ ያለው ሰላም መልካም ቢኾንም በአጎራባች አካባቢ የሚንቀሳቀሱ ኃይሎች ከሰላም ጎን እንዲቆሙ ከሀገር ሽማግሌዎች እና ከሃይማኖት አባቶች ጋር በመኾን ሰፊ ተግባራትን እያከናወኑ መኾናቸውን የተናገሩት ደግሞ የወረዳው ሰላም እና ጸጥታ ጽሕፈት ቤት ኀላፊው መሪጌታ ቃለጽድቅ ወልዴ ናቸው።

ይህ በመደረጉ የአካባቢውን መንገድ ለአገልግሎት ክፍት በማድረግ የሕዝብ ለሕዝብ ግንኙነቱን ወደነበረበት መመለስ መቻሉን ገልጸዋል። የስሃላ ሕዝብ ከአጎራባች ወረዳ ሕዝብ ጋር ተዋልዶ እና ተዛምዶ የሚኖር ሕዝብ ነው ብለዋል። ይህንንም አጠናክሮ ማስቀጠል እንደሚገባ ጠቁመዋል።

በ2017 ዓ.ም የሀገር ሽማግሌዎች እና የሃይማኖት አባቶች ለሰላም በከፈሉት ዋጋ ከ400 በላይ ታጣቂ ኃይሎች ወደ ሰላም መመለሳቸውን የገለጹት ደግሞ የብሔረሰብ አሥተዳደሩ ሰላም እና ጸጥታ መምሪያ ኀላፊ ሃምሳ አለቃ አዘዘው አዳነ ናቸው።

በተያዘው በጀት ዓመትም ከ100 በላይ ታጣቂዎች ለሕዝባቸው ሰላም ሲሉ መመለስ ችለዋል ያሉት ሃምሳ አለቃ አዘዘው “የሀገር ሽማግሌዎች እና የሃይማኖት አባቶች ለሰላም የሚከፍሉት ዋጋ ከፍተኛ ነው” ብለዋል።

ለሰላም የሚሰጠው የዋጋ መጠን የለውም ያሉት የመምሪያ ኀላፊው የዋግ ኽምራ ሕዝብ በእጁ የያዘውን ሰላም አጽንቶ ከመያዝ ባሻገር ወደ አጎራባች ዞኖች ሰላሙን ማስፋፋት ያስፈልጋል ነው ያሉት።

የአማራ ክልል መንግሥት ከአማራ ፋኖ ሕዝባዊ ድርጅት ጋር ያደረገው የሰላም ስምምነት ለክልሉ ብሎም ለሀገሪቱ ሰላም መጽናት የሚኖረው ፋይዳ የጎላ በመኾኑ የሀገሪቷን እድገት ለማስቀጠል ሁሉም ለሰላም ዘብ እንዲቆሙ አሳስበዋል።

ዘጋቢ፦ ደጀን ታምሩ

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleየአካል ጉዳተኞችን ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ እየሠራ ነው።
Next articleየተቋም ፍቅርን በሠራተኞች ላይ መገንባት እጅግ አስፈላጊ ነው።