የአካል ጉዳተኞችን ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ እየሠራ ነው።

10

ደብረ ብርሃን: ኅዳር 26/2018 ዓ.ም (አሚኮ) የአማራ ክልል ሴቶች፣ ወጣቶችና ማኅበራዊ ጉዳይ ቢሮ ኀላፊዎች በደብረ ብርሃን ከተማ አካል ጉዳተኞችን በኢኮኖሚ ተጠቃሚ ለማድረግ እየተሠሩ ያሉ ሥራዎችን ከሌሎች የክልል፣ የዞን እና የወረዳ አመራሮች ጋር በመኾን ተዘዋውረው ጎብኝተዋል።

የሴት አካል ጉዳተኞች፣ የስጋ ደዌ ተጠቂዎች እና መስማት የተሣናቸው ማኅበራት የተሰማሩባቸው የሥራ ዘርፎችም ጉብኝት ተደርጎባቸዋል። በማኅበራቱ የታቀፉ አባላት በተፈጠረላቸው የሥራ እድል እና ምቹ ሁኔታ በኢኮኖሚ ተጠቃሚ እየኾኑ እንደሚገኙ ገልጸዋል፡፡ ከአባላቱ ተጠቃሚነት ባሻገር ለሌሎች የሥራ እድል በመፍጠር እንዲኹም ለማኅበረሰቡ አገልግሎት መስጠት እንደቻሉም ተናግረዋል።

መንግሥት እና ረጅ ድርጅቶች የተለያዩ ድጋፎችን እያደረጉላቸው እንደኾነም ገልጸዋል፡፡ የብድር አቅርቦት፣ የገበያ ትስስር እና መስማት የተሳናቸው ማኅበር የሚጠቀምበት መሬት የይዞታ ማረጋገጫ በቀጣይ ትኩረት ቢሰጥባቸው ተብለው የተነሡ ጥያቄዎች ናቸው።

የክልሉ ሴቶች፣ ወጣቶችና ማኅበራዊ ጉዳይ ቢሮ ምክትል ኀላፊ ንጹህ ሸፈራው የደብረ ብርሃን ከተማ አሥተዳደር የአካል ጉዳተኞችን ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ አርዓያነት ያለው ሥራ እየሠራ ስለመኾኑ የሚያሳይ ተግባርን መመልከት ችለናል ብለዋል።

ቢሮው የአካል ጉዳተኞች መብት እንዲከበር፣ እኩል ተሣትፎ እና ውክልና እንዲያገኙ እንዲሁም ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነታቸው እንዲረጋገጥ በትኩረት እየሠራ እንደኾነም ተናግረዋል፡፡ በክልሉ ከ360 በላይ የአካል ጉዳተኞች ማኅበራት ተደራጅተዋል ብለዋል። አሁንም በቤት ውስጥ የቀሩ አካል ጉዳተኞች እንዲወጡ እና በማኅበራት ታቅፈው ተጠቃሚነታቸው መረጋገጥ እንዲችል የግንዛቤ ፈጠራ ላይ በትኩረት ሊሠራ ይገባል ብለዋል።

አካል ጉዳተኞች የሚያነሧቸው ጥያቄዎች በየደረጃው ምላሽ እንዲያገኙ እንደሚሠራም ገልጸዋል። የአካል ጉዳተኞች ቀን ክልላዊ ማጠቃለያ በደብረ ብርሃን ከተማ በተለያዩ ዝግጅቶች እየተከናወነ ይገኛል።

ዘጋቢ:- ሥነ ጊዮርጊስ ከበደ

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleየአማራ ሕዝብ ሙዚየም የግንባታ ሂደት እየተፋጠነ ነው።
Next articleየሀገር ሽማግሌዎች እና የሃይማኖት አባቶች ለሰላም እየከፈሉት ያለው ዋጋ የሚደነቅ ነው።