
በናይጀሪያ ፕሬዝዳንታዊ ምርጫ ፕሬዝዳንት ቡሃሪ እና የቀድሞው ምክትል ፕሬዝዳንት አቡበከር ዋነኛ ተፎካካሪ ሆነዋል፡፡
የዛሬ ሳምንት ናይጀሪያዊያን ፕሬዝዳንታቸውን ለመምረጥ ስዓታትን በሚጠብቁበት ወቅት የሀገሪቱ የምርጫ ቦርድ ጋዜጣዊ መግለጫ ሰጠ፡፡ በሀገሪቱ በነበረው ምቹ ያልሆነ የአየር ፀባይ ምክንያት የምርጫ ቁሳቁስ ወደ ጣቢያዎቹ ማድረስ አልቻልኩም በሚል ምክንያት ምርጫውን ማራዘሙንም አስታወቀ፡፡
ዛሬ ግን ከሰዓታት በፊት የምርጫ ሂደቱ በይፋ ተጀምሮ ናይጀሪያዊያን ርዕሰ ብሔራቸውን እየመረጡ ነው፡፡ የ76 ዓመቱ የሀገሪቱ ፕሬዝዳንት ሙሃመድ ቡሃሪ ዋና ተቀናቃኝ የ72 ዓመቱ የቀድሞው ምክትል ፕሬዝዳንት አቲኩ አቡበከር ናቸው፡፡
በአፍሪካ በነዳጅ ዘይት ምርቷ ግንባር ቀደምት እንደሆነች የሚነገርላት ናይጀሪያ በዘርፉ የምታገኘውን ጥቅም ሙስና እንደተፈታተነው ይነገራል፡፡ ማንም ይመረጥ ማን ናይጀሪያዊያን ቀጣዩ ርዕሰ ብሔር በኤሌክትሪክ ፍጆታ፣ በፀረ ሙስና ትግል፣ በፀጥታ ስጋቶችና በምጣኔ ሃብታዊ እንቅስቃሴ ላይ አተኩሮ እንዲሰራ ይጠብቃሉ፡፡
የእስላማዊ ታጣቂ ቡድን ቦኮሃራም ‹‹ስትራቴጅክ›› ቦታ እንደሆነች በሚነገርላት የቦርኖ ግዛት ከሁለት ሰዓት በፊት የምርጫ ሂደቱ ተጀምሯል፡፡ በዚህ ስፍራ ምርጫው መጀመሩን ያረጋገጠው የቢቢሲው ዘጋቢ የምርጫውን ሰላማዊ ሂደቶች ሊረብሹ የሚችሉ ሁኔታዎች ያጋጥማሉ ተብሎ ከሚያሰጉ ቦታዎች አንዱ መሆኑን ጠቁሟል፡፡
ለፕሬዝዳንታዊ ምርጫው 73 ተወዳዳሪዎች ቢመዘገቡም፤ በምረጡኝ ቅስቀሳው ወቅት ግን የሁለቱ ተወዳዳሪዎች ተሳትፎ ከፍተኛ ነበር፡፡ የፕሬዝዳንት ቡሃሪ ፓርቲ ኦል ፕሮግረሲቨ ኮንግረንስ ሀገሪቱን ወደ ተሻለ ደረጃ ለማሸጋገር እንደሚሰራ በምረጡኝ ቅስቀሳው ወቅት ቃል ገብቷል፡፡ ባለፉት አራት ዓመታት ፕሬዝዳንት ቡሃሪ ለሀገሪቱ ቀጣይ ዕድገት መሰረት ጥለዋል ያለው ፓርቲው በቀጣይም ይህን አጠናክሮ ለመቀጠል እንደሚሰራ ገልጿል፡፡
ዋና ተቀናቃኙ አቡበከር እና ፓርቲያቸው ፒፕልስ ዲሞክራቲክ ፓርቲ ባለፉት አራት ዓመታት ፕሬዝዳንት ቡሃሪና መንግስታቸው ያደበዘዟትን ናይጀሪያ እንደገና እንደሚሰሯት ቃል ገብተዋል፡፡
ከሰሜናዊቷ እና የእስላማዊ እምነት ተከታዮች ከሚበዙባት የናይጀሪያ አካባቢ እንደወጡ የሚነገርላቸው ሁለቱም ተፎካካሪዎች ከ1999 ጀምሮ በወታደራዊ ሃይል ተፅዕኖ ብዙም ያልራቀችውን ሀገር ወደ ዴሞክራሲያዊ እንቅስቃሴ ያሸጋግሯታል ተብሎ ይጠበቃል፡፡
በናይጀሪያ ለምርጫ ከተመዘገቡት ከ80 ሚሊየን መራጮች ውስጥ ከግማሽ በላይ የሚሆኑት ከ35 ዓመት በታች ናቸው፡፡ ፕሬዝዳንት ቡሃሪ ወደ ፕሬዝዳንትነት የመጡት በ2015 እንደነበር ይታዎቃል፡፡
ምንጭ፡- ቢቢሲ
በታዘብ አራጋው