
ባሕር ዳር: ኅዳር 26/2018 ዓ.ም (አሚኮ) የአማራ ሕዝብን ታሪክ ለትውልዱ የሚያስተዋውቅ፣ የሚዘክር እና የተዛቡ ትርክቶችን በማረም የተለያዩ ምርምሮችን ማከናወን እንዲያስችል ኾኖ እየተሠራ ያለው የአማራ ሕዝብ ሙዚየም ግንባታ እየተፋጠነ መኾኑን የክልሉ ባሕል፣ ቱሪዝም እና ስፖርት ቢሮ አስታውቋል።
የክልሉ ባሕል፣ ቱሪዝም እና ስፖርት ቢሮ ምክትል ኀላፊ አየለ አናውጤ (ዶ.ር) በመገንባት ላይ የሚገኘው ሙዚየሙ ጠቅላላ ይዞታው 15 ሺህ ካሬ መሬት ነው ብለዋል። ሕንጻው 8 ሺህ ካሬ ሜትር ላይ እንዳረፈም ገልጸዋል።
የአማራ ሕዝብ በኢትዮጵያ ሀገረ መንግሥት ምሥረታ ያበረከተው አስተዋጾኦ ከፍተኛ ነው ያሉት ዶክተር አየለ ይህ ሕዝብ በርካታ ታሪክ፣ ቅርስ እና ባሕል ያለው መኾኑንም አንስተዋል። የአማራ ሕዝብ ታሪኩ በተደራጀ መልኩ ከትውልድ ወደ ትውልድ እንዲተላለፍ የሚያስችል ጥናት እና ምርምር የሚደረግበት ሙዚየም አልነበረውም ነው ያሉት።
የክልሉ መንግሥትም ችግሩን በማየት “1 ነጥብ 2 ቢሊዮን ብር መድቦለት የሙዚየም ግንባታው እየተከናወነ ነው” ብለዋል። የሙዚየም ግንባታው ሲጠናቀቅም የክልሉ ሕዝብ ታሪክ፣ ኪነ ጥበብ፣ ባሕል፣ ተፈጥሯዊ ጸጋ እና ቅርሶች ይተዋወቁበታል ነው ያሉት።
ሙዚየሙ ከ110 በላይ ክፍሎች ያሉት ሲኾን የዲጂታል ሙዚየምም መካተቱን ነው ዶክተር አየለ የተናገሩት። የሙዚየሙ ግንባታው አሁን ላይ በጥሩ ሁኔታ ላይ ይገኛል ያሉት ዶክተር አየለ በዚህ ዓመትም የሕንጻው የስትራክቸር ሥራዎች ይጠናቀቃል ነው ያሉት። በቀጣይም የሙዚየሙ ውስጣዊ ሥራዎች እንደሚጠናቀቁ ገልጸዋል።
ግንባታውን የሚያከናውነው የዘመን ኮንስትራክሽን ኮርፖሬሽን ዋና ሥራ አሥፈጻሚ ታደሠ ግርማ ግንባታው በ2015 ዓ.ም መጨረሻ ላይ መጀመሩን ተናግረዋል። ባለፉት ዓመታት ክልሉ የገጠመው የጸጥታ ችግር በግንባታው ሂደት ላይ አሉታዊ ተጽዕኖ ማሳረፉንም ገልጸዋል።
አሁን ላይ ግን ሁኔታዎች ስለተስተካከሉ ግንባታው በጥሩ ደረጃ ላይ እየተከናወነ ይገኛል ነው ያሉት። በቂ ግብዓት ቀርቧል፤ የሰው ኃይልም ተሠማርቷል፤ በፈረቃ ጭምር ለመሥራት እየተነጋገርን እንገኛለን ብለዋል።
ፕሮጀክቱ በቅንጅት እየተከናወነ በመኾኑ የስትራክቸር ሥራው በዚህ በጀት ዓመት እንደሚጠናቀቅ ነው ዋና ሥራ አሥፈጻሚው የተናገሩት።
በልህቀት ዲዛይን እና ቁጥጥር ኮርፖሬሽን የፕሮጀክቱ ተቆጣጣሪ መሐንዲስ አዳነ አምሳሉ ግንባታው ጥራቱን ጠብቆ እንዲሠራ ግብዓቶችን በቤተ ሙከራ ይፈተሻሉ ብለዋል። የአርማታ ሥራው ክትትል ይደረግበታል ነው ያሉት። በጠቅላላው ሥራው በጥራት እየተከናወነ ነው ብለዋል።
ዘጋቢ:- ሙሉጌታ ሙጨ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
