
ደባርቅ፡ ኅዳር 26/2018 ዓ.ም (አሚኮ) እየተሠሩ ያሉ የግንዛቤ ፈጠራ ሥራዎች ተጨባጭ የአስተሳሰብ ለውጥ ለማምጣት አጋዥ መኾናቸውን የሰሜን ጎንደር ዞን አካል ጉዳተኞች ማኅበራት ፌዴሬሽን ገልጿል።
ማኅበሩ “አካል ጉዳተኝነትን የሚያካትት ማኅበረሰብ መገንባት ለተሻለ ማኅበራዊ ዕድገት” በሚል መሪ መልዕክት በሀገር አቀፍ ደረጃ ለ33ኛ ጊዜ የሚከበረውን የአካል ጉዳተኞች ቀንን በተለያዩ መርሐ ግብሮች አክብሯል።
በመርሐ ግብሩ መልዕክት ያስተላለፉት የሰሜን ጎንደር ዞን ሴቶች፣ ሕጻናት እና ማኅበራዊ ጉዳይ መምሪያ ኀላፊ ባንችዓምላክ መልካሙ የአካል ጉዳተኞችን ሁለንተናዊ ተጠቃሚነት እና ተሳትፎ ለማሳደግ የተለያዩ ተግባራት እየተከናዎኑ መኾኑን ገልጸዋል።
አካል ጉዳተኝነት ከአቅም እና ችሎታ ማነስ ጋር የሚገናኝ ባለመኾኑ አካል ጉዳተኞችን መደገፍ እና ለተሻለ ለውጥ ማበረታታት እንደሚገባ ተናግረዋል። የሰሜን ጎንደር ዞን የአካል ጉዳተኞች ማኅበራት ፌዴሬሽን ፕሬዝዳንት ዝማም አቡሃይ የአካል ጉዳተኞች ማኅበራት ለተወከሉላቸው አባላት ድምጽ በመኾን መብታቸውን ለማስከበር እየተንቀሳቀሱ እንደሚገኝ ገልጸዋል።
በዞኑ ከ20 ሺህ በላይ አካል ጉዳተኞች ይኖራሉ ተብሎ እንደሚገመት የተናገሩት ወይዘሮ ዝማም ከተለያዩ አጋር ተቋማት ጋር በመተባበር የሥልጠና እና የቁሳቁስ ድጋፍ ለማድረግ እየተሠራ እንደኾነም አብራርተዋል።
በተሠሩ የግንዛቤ ፈጠራ እና ሌሎች መሰል ሥራዎች ለውጥ የመጣ ቢኾንም በርካታ ቀሪ ጉዳዮች በመኖራቸው ሁሉም ባለድርሻ አካል ርብርብ ሊያደርግ እንደሚገባ አስገንዝበዋል። የአካል ጉዳተኞች ፍትሐዊ ተጠቃሚነት በተለይም በትምህርት ዘርፍ ለማረጋገጥ የአካል ጉዳተኞች ማኅበራት በትኩረት እየሠሩ ነው ብለዋል።
የመድረኩ ተሳታፊዎችም የአካል ጉዳተኞች ቀን መከበሩ የግንዛቤ ፈጠራ ሥራ ለመሥራት እና የአካል ጉዳተኞችን ተሰጥኦ ለማውጣት ብሎም ለማዳበር እንደሚያግዝ ጠቁመዋል።
አካል ጉዳተኞች በአንድ መወያየት እና መምከራቸው በቀጣይ የሚሠሩ የጋራ ሥራዎች ላይ ዕቅድ ለማዘጋጀት እና በጋራ ተንቀሳቅሶ ለማስፈጸም አቅም ይፈጥራል ነው ያሉት።
ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ለአካል ጉዳተኞች የሚሰጡ ትኩረቶች መሻሻላቸውን ገልጸው በቀጣይም ተጠናክረው መቀጠል እንዳለባቸውም ጠቁመዋል።
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
