የሕዝብን ጥያቄ ለመፍታት መሪዎችን በዕውቀት እና በክህሎት ማሳደግ ያስፈልጋል።

13

ገንዳ ውኃ፡ ኅዳር 26/2018 ዓ.ም (አሚኮ) በምዕራብ ጎንደር ዞን ”በመደመር መንግሥት ዕይታ፣ የዘርፎች ዕምርታ” በሚል መሪ መልዕክት ለወረዳ እና ለከተማ አሥተዳደር የሥራ ኀላፊዎች ሥልጠና መሥጠት ተጀምሯል።

ሥልጠናው በተግባር የታገዘ የንድፈ ሃሳብ ትንተና እና በተለያዩ ጉዳዮች ዙሪያ ምክክር እንደሚደረግ ተመላክቷል። ሥልጠናው ለዘጠኝ ቀናት እንደሚቆይ የተገለጸ ሲኾን በሥልጠናው ሀገራዊ እና ክልላዊ ዋና ዋና ጉዳዮች ተካትተዋል ተብሏል።

የምዕራብ ጎንደር ዞን ዋና አሥተዳዳሪ እያሱ ይላቅ በመክፈቻው ላይ ሥልጠናው የጋራ አቋምን ለማጽናት ያግዛል ብለዋል። ሥልጠናው ዘላቂ ሰላም እና ልማትን ለማረጋገጥ የተጀመሩ የልማት ሥራዎችን ለማጎልበት እንደሚያግዝም አስገንዝበዋል።

“የግብርና እና የገጠር ትራንስፎርሜሽን ዕመርታ፣ የከተማ ልማት ዘርፍ ዕመርታ፣ የኢንዱስትሪ ዘርፍ እመርታ እና የቱሪዝም ዘርፍ እመርታ” በሚሉ ዋና ዋና ጉዳዮች ትኩረት ያደረገ ሥልጠና መኾኑንም አብራርተዋል።

ብልጽግና ፓርቲ የሀገሪቱን ዕድገት ዕውን ለማድረግ ዘርፈ ብዙ ሥራዎችን ለማከናወን እየተሠራ መኾኑንም ጠቁመዋል። የሕዝብን ጥያቄ ለመፍታት መሪዎች በዕውቀት እና በክህሎት ማሳደግ እንደሚያስፈልግም ዋና አሥተዳዳሪው ተናግረዋል።

በብልጽግና ፓርቲ የምዕራብ ጎንደር ዞን ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት ኀላፊ እንዳለው ማሩ ሥልጠናው ለወደፊቱ ለውጥ ለማምጣት የሚያስችሉ ሃሳቦች ይነሱበታል ብለዋል። ሥልጠናው በተግባር የታገዘ እና ለውጤት መነሳሳትን ለመፍጠር የሚያግዝ እንደኾነም አስረድተዋል።

ሥልጠናው የሥራ ኀላፊዎች በተለያዩ ጉዳዮች ላይ ተቀራራቢ የግንዛቤ ደረጃ እንዲኖራቸው እና አስተሳሰባቸውን እንዲያጎለብቱ የሚያግዝ መኾኑንም ገልጸዋል። የሥልጠናው ተሳታፊዎች በበኩላቸው የሚወስዱት ሥልጠና የዕውቀት አቅማቸውን እና አመለካከታቸውን እንደሚያሰፋላቸውም ተናግረዋል።

በሥልጠናው የሚቀስሙትን ዕውቀት ተጠቅመው ማኅበረሰባቸውን ለማገልገል ከወዲሁ የነቃ ተሳትፎ ለማድረግ ዝግጁ መኾናቸውንም ገልጸዋል።

ዘላቂ ሰላም እና ልማትን ማረጋገጥ በሚቻልባቸው ጉዳዮች ዙሪያ አሁን ከሚሰጠው ሥልጠና የተለያዩ ንድፈ ሃሳባዊ ትምህርቶችን በመቅሰም ወደ ተግባር ለመግባት ጥረት እንደሚያደርጉም አስገንዝበዋል።

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous article“ሰላም ሐቀኛ ውይይትን ይፈልጋል” ምክትል ርእሰ መሥተዳደር አብዱ ሁሴን (ዶ.ር)
Next articleየሕዝብን ጥያቄ ለመፍታት መሪዎችን በዕውቀት እና በክህሎት ማሳደግ ያስፈልጋል።