
ባሕር ዳር፡ ሰኔ 14/2012 ዓ.ም (አብመድ) የኢፌዴሪ ጦር ኃይሎች ጠቅላይ አዛዥ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ አህመድ (ዶክተር) ለመከላከያ ሠራዊት ጄነራል መኮንኖች የስትራቴጂ ሰነዱን በተመለከተ ዛሬ ገለጻ አድርገዋል።
ሰነዱ ወቅታዊ አገራዊ ፈተናዎችን ባገናዘበ መልኩ ዓለም አቀፋዊ የወታደራዊ አቅምን መሠረት አድርጎ መዘጋጀቱንና ለሕገ መንግሥቱ ተገዢ የሆነና ለሕዝብና ለአገር ዘብ የቆመ ሠራዊት ለመገንባት እንደሚያግዝ ጠቅላይ ሚኒስትሩ አስረድተዋል።
የካቲት 2012 ዓ.ም ላይ የታተመው ረቂቅ የስትራቴጂክ ሰነዱ በሂደት እየዳበረ ሁሉም ዜጋ በቀላሉ እንዲረዳው፣ እንዲያውቀውና በጊዜ ሂደት ከወቅቱ ጋር እየተናበበ እንዲሻሻል ተደርጎ የሚቀረጽ መሆኑን የተናገሩት ዶክተር ዐብይ በአዲስ መልክ ለማዘጋጀት ያስፈለገው ሠራዊቱን ለማዘመን በማለም እንደሆነ አስገንዝበዋል።
የሠራዊት ግንባታ ስትራቴጂው የአገሪቱን ሉዓላዊነት ባስከበረ መልኩ ሕዝቦቿ የሚተማመኑበት፣ ዳር ድንበሯን የሚያስከብርና ዓለምአቀፍ ተቀባይነቷ እንዲጨምር በሚያስችል መልኩ መዘጋጀቱንም አስረድተዋል።
የመከላከያ ሠራዊቱ ለፓርቲ፣ ለብሔርና ለቡድን የወገነ ሳይሆን አገራዊ ሉዓላዊነትን መሠረት አድርጎ በሕገ መንግሥቱ የሚመራ ሆኖ አገራዊ ቀጣይነትን ማረጋገጥ እንዳለበትም ጠቅላይ ሚኒስትሩ አስገንዝበዋል።
ኢዜአ እንደዘገበው ውይይቱ በቀጣይም በተዋረድ እንደሚካሄድ ታውቋል።
