
ባሕር ዳር፡ ኅዳር 26/2018 ዓ.ም (አሚኮ) የባሕር ዳር ከተማ አሥተዳደር የኮሪደር ልማት አንድ አካል የኾነው የአልማ – ዋተር ፍሮንት ፕሮጀክት የመጨረሻው ምዕራፍ የግንባታ ሥራ እየተከናወነ ነው።
የአካባቢው ነዋሪ የኾኑት አቶ ግርማ ጥላሁን የአልማ – ዋተር ፍሮንት ፕሮጀክት ከመጀመሩ በፊት አካባቢው የታፈነ፣ የፈራረሰ እና ለእንቅስቃሴም ምቹ እንዳልነበር ነው የሚናገሩት።
መንገዱ እና የኮሪደር ልማቱ በመሠራቱ ደስተኛ መኾናቸውን ተናግረዋል። ሰው እንደ ፈለገው እንዲንቀሳቀስ እና የተሻለ አየር እንዲያገኝ የሚያስችል ነው ብለዋል።
በከተማዋ እየተከናወነ ያለው አጠቃላይ የኮሪደር ልማትም ጣናን በብዙ ቦታ የገለጠ፣ የመዝናኛ መናፈሻዎች የተገነቡበት በመኾናቸው ሰው እንደፈለገው ለመዝናናት ዕድል ፈጥሯል ይላሉ።
በሬማ ኮንስትራክሽን የአልማ – ዋተር ፍሮንት የመንገድ ፕሮጀክት ማናጀር አቤኔዘር ማስረሻ ፕሮጀክቱ 800 ሜትር ርዝመት እና 40 ሜትር ስፋት እንዳለው አብራርተዋል። በመንገዱ በሁለቱም በኩል ግሪነሪ፣ እግረኛ መንገድ እና የብስክሌት መንገድን እንደሚያካትት ገልጸዋል።
የመንገድ ፕሮጀክቱ በግንቦት 2017 ዓ.ም መጀመሩን ተናግረዋል። በአሁኑ ወቅት የፕሮጀክቱ የመጨረሻ ምዕራፍ የኾነው የግንባታ ሥራ እየተከናወነ መኾኑን ጠቁመዋል። በቀን በአማካኝ ለ200 ሰዎች የሥራ ዕድል እፈጠረ ስለመኾኑም ተናግረዋል። እስከ ታኅሣሥ 30/2018 ዓ.ም ፕሮጀክቱን አጠናቅቆ ለማስረከብ እየተሠራ ነውም ብለዋል።
የባሕር ዳር ከተማ አሥተዳደር ከተማ እና መሠረተ ልማት መምሪያ ኀላፊ ተሻገር አዳሙ በከተማዋ በመጀመሪያው ዙር ደረጃውን የጠበቀ የ2 ነጥብ 5 ኪሎ ሜትር የኮሪደር ልማት ሥራ ተሠርቶ መጠናቀቁን አስታውቀዋል።
6 ነጥብ 1 ኪሎ ሜትር የሚሸፍነው ሁለተኛው ዙር የኮሪደር ልማትም እየተከናወነ ነው ብለዋል። የአልማ ዋተር ፍሮንት የኮሪደር ልማትም የሁለተኛው ዙር የኮሪደር ልማት አካል መኾኑን ነው የተናገሩት።
የኮሪደር ልማቱ ለሕዝቡ ተጨማሪ የመዝናኛ አማራጮችን ይዞ የመጣ መኾኑንም አብራርተዋል። የጣና ነፋሻማ አየር ወደ ከተማዋ እንዲገባ ያደረገ ስለመኾኑም ጠቁመዋል።
ልማቱ ለበርካታ ሰዎች የሥራ ዕድል መፍጠሩንም ገልጸዋል። በ2017 በጀት ዓመት ከ29 ሺህ በላይ ዜጎች የሥራ ዕድል መፍጠሩን ለአብነት አንስተዋል። በተሠሩት የካፍቴሪያ እና የመዝናኛ ቦታዎች በርካታ ወጣቶች የሥራ ዕድል እየተፈጠረላቸው ነው ብለዋል።
የኮሪደር ልማቱ በአጭር ጊዜ ፕሮጀክትን የመፈጸም አቅምን አሳድጓል፣ አዲስ የሥራ ባሕልን አምጥቷል ነው ያሉት። ከተማዋን ሳቢ እና ማራኪ በማድረግ እና ገጽታን በመገንባት ጎብኝዎችን ለመሳብም ሚናው የጎላ ስለመኾኑ አስረድተዋል።
ማኅበረሰቡ ለኮሪደር ልማቱ ሃሳብ ከመስጠት ጀምሮ በጉልበት እና በገንዘቡ ጭምር ከፍተኛ ድጋፍ እያደረገ እንደሚገኝም ገልጸዋል።
ዘጋቢ: አሰፋ ልጥገበው
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
