
ባሕር ዳር፡ ኅዳር 26/2018 ዓ.ም (አሚኮ) ባለታሪካችን ወይዘሮ አበበች ጎዴነው ትውልድ እና እድገታቸው በደቡብ ጎንደር ዞን ነው። ወይዘሮ አበበች የሁለት ልጆች እናት አንደኾኑ የነበራቸውን የትዳር ሕይዎት በምልሰት ነገሩን።
ወይዘሮዋ ትዳር የያዙት በራሳቸው ፍላጎት እንዳልነበር እና ቤተሰብ ጫና አድርጎ ጎጆ እንዲቀልሱ እንዳደረጋቸውም ይናገራሉ። ትዳር ወደው እና ፈቅደው ሲኾን ጣፋጭ ነው ያሉት ወይዘሮዋ ከፍላጎት ውጭ ሲኾን ደግሞ የዚያኑ ያክል መራራ ነው ብለዋል። ትዳር ከተያዘ በኋላ ያለውም ሕይዎት በሕይዎት አጋር ባለ ግንኙነት ሊሰምር አለያም ሊበላሽ ይችላልም ይላሉ።
ወይዘሮዋ አበበች ጎዴነው ምንም እንኳን ከፍላጎታቸው ውጭ ያገቡ ቢኾንም ጎጆን የሕይዎት አጋራቸው ወደ ጣፋጭ ሕይዎት መቀየራቸውንም ያስታውሳሉ። በወቅቱ በትዳራቸው መቻቻል እና መከባበር እንዲኖር በማድረጋቸው ትዳሩ ልጆች እንዲፈሩበት ማድረጋቸውንም ጠቁመዋል።
ይሁን እንጅ ጎጇቸው ቀስ እያለ ወደ ጭቅጭቅ እና አለመግባባት እየተለወጠ መጣ የሚሉት ወይዘሮዋ ባለቤታቸው ከጭቅጭቅ አልፎ ውጭ አምሽቶ መምጣት እና አካላዊ ጠቃት ማድረስ መጀመራቸውን አስረድተዋል።
በዚህ ምክንያትም ደስታ ከቤታቸው የጠፋው ወይዘሮዋ ሽማግሌወችን ሠብሥበው ፍች ፈጽመው ኑሯቸውን ወደ ባሕር ዳር ማድረጋቸውን ነግረውናል። የግል ሥራ እየሠሩም ልጆቻቸውን እንዳስተማሩ ጠቁመዋል።
ፆታን መሠረት ያደረገ ጥቃት ላይ ዕውቅናው እንዳልነበራቸው የሚናገሩት ወይዘሮዋ ፆታን መሠረት ያደረገ ጥቃት አስገድዶ መድፈር ብቻ አድርገው ያዩ እንደነበርም ነግረውናል።
👉ለመኾኑ ፆታን መሠረት ያደረገ ጥቃት ምንድን ነው? በአማራ ክልል የሴቶች፣ ወጣቶች እና ማኅበራዊ ጉዳይ ቢሮ ምክትል ኅላፊ ዝና ጌታቸው ሥርዓተ ፆታን መሠረት ያደረገ ጥቃት ማለት በማንኛውም መልኩ ሥርዓተ ፆታዊ ሚናን መሠረት አድርጎ በሴቶች እና ሕጻናት ላይ የሚፈፀም ጥቃት ነው ብለዋል፡፡
ጥቃቱ አካላዊ፣ ወሲባዊ፣ ሥነ ልቦናዊ አና ኢኮኖሚያዊ ጥቃትን አጠቃሎ የያዘ ሲኾን ከግለሰብ ፈቃድ ውጭ የሚፈፀም ጎጂ ኢሰብዓዊ ድርጊት ነው ብለውታል ምክትል ኀላፊዋ ሥርዓተ ፆታን መሠረት ያደረጉ የጥቃት አይነቶች የሚባሉት አካላዊ፣ ወሲባዊ፣ ሥነልቦናዊ፣ ኢኮኖሚያዊ እና ማኅበራዊ ጎጅ ልማዳዊ ድርጊቶች ናቸው ብለዋል።
👉ፆታን መሠረት ያደረጉ ጥቃቶች የሚያስከትሏቸው ችግሮች ምንድን ናቸው? ምክትል ኅላፊዋ ዝና ጌታቸው እንደተናገሩት ጾታዊ ጥቃት የደረሰባት ሴት የተለያዩ የጤና፣ የማኅበራዊ እና የሥነ ልቦናዊ ችግሮች ይደርሱባታል።
ጾታዊ ጥቃት የደረሰባት ሴት የስሜት መጎዳት፣ የሞራል ውድቀት፣ የፍርሀት ስሜት፣ ብስጩነት፣ እራስን መጥላት፣ ሀፍረት እና በራስ አለመተማመን ችግር በከፍተኛ ሁኔታ ያጋጥማታል ነው ያሉት። ጥቃት የደረሰባቸው ሴቶች እና ሕጻናት ለጭንቀት የተጋለጡም ናቸው ብለዋል፡፡
👉ለመኾኑ ለሥርዓተ ፆታ መሠረት ያደረገ ጥቃት ዋና ዋና መንስኤዎች ምንድን ናቸው? ምክትል ኀላፊዋ ዝና ለሥርዓተ ፆታ መሠረት ያደረገ ጥቃት ዋና መንስኤዎቹ የወንዶች የበላይነት አስተሳሰብ፣ የሥርዓተ ፆታ አመለካከት መዛባት፣ የኀይል አለመመጣጠን እና ለሰብዓዊ መብቶች ትኩረት አለመስጠት ዋነኞቹ መንስኤዎች ናቸው ብለዋል።
👉ፆታን መሠረት ያደረጉ ጥቃቶችን የሚያባብሱ ሁኔታዎችስ? እንደ ምክትል ኀላፊዋ ገለፃ የማኅበረሰቡ የግንዛቤ ችግር አለማደግ፣ ሴቶች በኢኮኖሚ ራሳቸውን አለመቻል፣ ተገቢ ያልኾነ ወግ እና ልማድ፣ የሴቶች ጥቃትን አንዳንዴ እንደ ፍቅር መገለጫ አድርጎ መቁጠር፣ ኅብረተሰቡ መረጃ እና ማስረጃ የመስጠት ፍላጎቱ አናሳ መኾን፣ የፍትሕ ውሳኔዎች አስተማሪ አለመኾናቸው ጥቃቶች እንዲባባሱ ማድረጋቸውን አንስተዋል።
👉ፆታን መሠረት ያደረጉ ጥቃቶችን እንዴት መከላከል ይቻላል? ፆታን መሠረት ያደረጉ ጥቃቶችን መከላከል የሚቻለው መጀመሪያ ሁሉም የሚመለከታቸው አካላት ጥቃት የሚያደርሰውን ጉዳት በውል በመገንዘብ እና በቅንጅት በተደራጀ አግባብ መሥራት ሲችሉ ነው ብለዋል ምክትል ኀላፊዋ።
በተለይ ጥቃት የሚያደርሰውን አካል ጉዳት እና ወንጀል መኾኑን ማስገንዘብ እጅግ ወሳኙ ተግባር መኾኑን ገልጸዋል። በጉዳዩ ላይ ለሚሠሩ መሪዎች፣ ለባለሙያዎች፣ ለሃይማኖት አባቶች እና ለተፅዕኖ ፈጣሪ ግለሰቦች አስፈላጊውን ሥልጠና በመስጠት ወደ ሥራ ማስገባትንም በመፍትሄነት አንስተዋል።
በየደረጃው ያለው መሪ በባለቤትነት ይዞ መሥራት ሲችል፣ የሚመለከታቸው አካላት በተቀናጀ እና በጋራ መሥራት ሲችሉ፣ አጥፊዎች ላይ አስተማሪ እርምት መውሰድ ሲቻል እና ተገቢውን ግንዛቤ ለማኅበረሰብ ማስጨበጥ ሲቻል ጥቃቱን መከላከል ይቻላል ነው ያሉት።
የክልሉ ወጣቶች እና ማኅበራዊ ጉዳይ ቢሮም ጾታን መሠረት ያደረገ ጥቃትን ለመከላከል በሰፊው እየሠራ መኾኑን ጠቁመዋል። ጥቃትን ለመከላከል የመደበኛ ዕቅድ አካል አድርጎ መሥራት እንደሚገባም አብራርተዋል።
ዘጋቢ፦ ሰመሀል ፍስሀ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
