
ባሕር ዳር: ኅዳር 25/2018 ዓ.ም (አሚኮ) የበጋ መስኖ ስንዴ ማምረት እንደ ሀገር በምግብ ራስን ለመቻል እና ከውጭ የሚገባውን የስንዴ ምርት ለመተካት በትኩረት እየተሠራበት ይገኛል፡፡
በአማራ ክልልም በመስኖ ከሚለማው መሬት አብዛኛውን ድርሻ ስንዴ እንዲለማበት እየተደረገ ነው።
አርሶ አደር ስዩም አግዜ በሰሜን ሸዋ ዞን የበጋ መስኖ ስንዴ አምራች ናቸው። አካባቢያቸው ለመስኖ ምቹ መኾኑን እና ለዘንድሮው ዓመት የማምረት ሥራ ዝግጅት ማድረጋቸውን ተናግረዋል፡፡
በግብርና ባለሙያዎች በኩል ውጤታማ የሚያደርጋቸውን የባለሙያ ድጋፍ፣ የምርጥ ዘር እና ማዳበሪያ አቅርቦት እንዳገኙም አንስተዋል። የበጋ መስኖ ስንዴ ምርት የተሻለ ማምረት ከተቻለ በሄክታር እስከ 40 ኩንታል የስንዴ ምርት ይገኛል ብለዋል።
አሁን የመስኖ ዘር ወቅት ነው ያሉት አርሶ አደር ስዩም እርሻ ተዘጋጅቶ እየተዘራ መኾኑን ገልጸዋል። የማዳበሪያ አቅርቦት የሚፈለገውን ያህል ባይኾንም ሁሉም እንዲያገኝ ይደረጋል ነው ያሉት።
የበጋ መስኖ ስንዴ ልማት አርሶ አደሮችን ተጠቃሚ የሚያደርግ ነው ብለዋል፡፡ አሁን ላይ ለስንዴ ምርት የግሪሳ ወፍ ስጋት እንደፈጠረባቸው ተናግረዋል፡፡
በሰሜን ሸዋ ዞን ግብርና መምሪያ የአትክልት እና ፍራፍሬ መስኖ ውኃ አጠቃቀም ቡድን መሪ አስካለ ይፍሩ በዞኑ የበጋ መስኖ ስንዴ በተያዘው የምርት ዘመን 50 ሺህ 500 ሄክታር መሬት ለማልማት መታቀዱን አንስተዋል።
በዞኑ በሁሉም ወረዳዎች አቅሙ ቢለያይም ስንዴ የሚመረት በመኾኑ እቅዱን ለመፈጸም አርሶ አደሮች፣ ባለሙያዎች እና መሪዎች ላይ የንቅናቄ ሥራ መሠራቱን ገልጸዋል።
በዚህ ወቅት የእርሻ እና የመስኖ ሥራ ላይ እንደኾኑም አንስተዋል፡፡ ማዳበሪያ በቂ ክምችት አለ፤ ወደ ወረዳዎች ፍላጎትን መሠረት አድርጎ መደልደሉን ተናግረዋል፡፡ ወደ አርሶ አደሮች በአግባቡ ለማድረስ ክትትል እንደሚደረግምም ገልጸዋል፡፡
ምርጥ ዘር አርሶ አደሮች በልውውጥ እና በግዥ እንዲያገኙ ተደርጓል ብለዋል። የግሪሳ ወፍ በየአካባቢው ባልታሰበ ጊዜ ይከሰታል፣ ከክልሉ እና ከፌዴራል ግብርና ሚኒስቴር ጋር በመተባበር ኬሚካል ርጭት እንደሚደረግ ተናግረዋል፡፡ የስንዴን ምርት የገበያ ችግር እንደሌለም አንስተዋል፡፡
የበጋ መስኖ ስንዴ ምርት ውጤታማ መኾኑን የገለጹት ቡድን መሪዋ ውኃ ተመጥኖ መሰጠቱ፣ በድግግሞሽ እርሻ መሠራቱ፣ ከተባይ እና በሽታ ነጻ እና በአጭር ጊዜ የሚደርስ በመኾኑ ውጤታማ ነው ብለዋል።
በአማራ ክልል ግብርና ቢሮ የመስኖ እና ሆርቲካልቸር ልማት ዳይሬክተር ይበልጣል ወንድምነው በ2018 የምርት ዘመን 350 ሺህ ሄክታር በበጋ መስኖ ስንዴ ለማልማት እቅድ ተይዟል ብለዋል፡፡
ከዚህም 13 ሚሊዮን ኩንታል ምርት ለማግኘት መታቀዱን አንስተዋል።
ለውጤታማነቱም የዘር ወቅት ቀደም ብሎ ከታኅሣሥ 15 በፊት ለማጠናቀቅ እየተሠራ ነው፣ ምክንያቱም በበጋ ወቅት ከፍተኛ ሙቀት በሚኖርበት ጊዜ የስንዴ ምርታማነት ላይ ተጽዕኖ ስለሚያሳድር ነው ብለዋል።
ለዚህም ለዞኖች የእቅድ ትውውቅ፣ የግንዛቤ ፈጠራ፣ እስከ መስኖ መሠረተ ልማት ድረስ በመስከረም ወር ተጠናቅቋል ነው ያሉት። ለስንዴ ልማት የሚያስፈልጉ ግብዓቶችን የመለየት እና ፈጻሚዎችን የማዘጋጀት ሥራዎች ተሠርተዋል ብለዋል።
ከ500 ሺህ ኩንታል በላይ ምርጥ ዘር ይጠይቃል ያሉት ዳይሬክተሩ 99 በመቶ አርሶ አደሮች በመኸር ከዘሩት እና ሌሎች ስንዴ ከዘሩ አካባቢዎች ላይ የዘር ልውውጥ እንዲያደርግ የጋራ መግባባት ላይ ተደርሷል ነው ያሉት። ከዘር አምራች ዩኒዬኖች የግብዓት አቅርቦት እንዲመቻች ስለመሠራቱም እንስተዋል፡፡
ማዳበሪያን በሚመለከት 580 ሺህ ኩንታል ማዳበሪያ የሚያስፈልግ ሲኾን ለዚህ የሚኾን የከረመ 1 ነጥብ 1 ሚሊዮን ኩንታል ማዳበሪያ መኖሩን ተናግረዋል፡፡ በቂ የማዳበሪያ አቅርቦት ስላለ ለአርሶ አደሮች የሚደርስበትን ሁኔታ ለማመቻቸት በወቅቱ የማዘዋወር ሥራ እየተሠራ ነው ብለዋል።
ካለፉት ዓመታት የበጋ መስኖ ስንዴ ልማት ወቅቱን ያልጠበቀ ዝናብ ችግር ነበር፤ ይህንን የዘር ወቅቱን በማስተካከል አየተፈታ ነው።
የበሽታ እና ተባይ ቁጥጥር ላይ የስንዴ ዋግ እና የተባይ ችግሮች እንዳጋጠሙም ተናግረዋል፡፡ ለዚህም የተባይ አሰሳ ግብረ ኃይል ሥራውን እንዲያከናውን አስፈላጊ ግብዓቶች የቀረቡ በመኾኑ የተባይ አሰሳ እና የመከላከል ሥራዎች እየተሠሩ ይገኛል ነው ያሉት።
የበጋ መስኖ ስንዴ ከተጀመረበት ጀምሮ በየዓመቱ የሚለማው መሬት ሽፋን እየጨመረ መጥቷል ብለዋል። በመንግሥት በኩልም ለመስኖ ሥራው የሚደረገው ድጋፍ ጨምሯል፤ አርሶ አደሮችም ተጠቃሚ እየኾኑ ነው ብለዋል።
አማካይ ምርታማነት በሄክታር ከ34 ኩንታል ወደ 40 ኩንታል ለማሳደግ እየተሠራ መኾኑንም ገልጸዋል።
ዘጋቢ፦ ፍሬሕይወት አዘዘው
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
