የመስኖ ምርታማነትን ለማሳደግ ቴክኖሎጂዎችን ጥቅም ላይ ለማዋል እየተሠራ ነው።

11

እንጅባራ፡ ኅዳር 25/2018ዓ.ም (አሚኮ) የአዊ ብሔረሰብ አሥተዳደር የ2018 በጀት ዓመት የበጋ መስኖ ስንዴ ልማት ማስጀመሪያ መርሐ ግብርን በባንጃ ወረዳ ሰንከሳ ቀበሌ አካሂዷል።

የዘር ሥራውን ያስጀመሩት የአዊ ብሔረሰብ አሥተዳደር ምክትል አሥተዳዳሪ እና የከተማ እና መሠረተ ልማት መምሪያ ኀላፊ አይተነው ታዴ የመስኖ ስንዴ ልማት የምግብ ዋስትናን ከማረጋገጥ ባሻገር ሀገሪቱን ከተረጂነት የማላቀቅ እና ሉዓላዊነትን የማስከበር ጉዳይ ነው ብለዋል።

የብሔረሰብ አሥተዳደሩን የመስኖ ምርታማነት ለማሳደግ ጊዜ ቆጣቢ እና ምርታማነትን የሚጨምሩ ቴክኖሎጂዎች ጥቅም ላይ ለማዋል እየተሠራ መኾኑንም አንስተዋል።

በዚህ ዓመት የእርሻ ሜካናይዜሽንን ለመተግበር የሚያስችሉ 100 ትራክተሮችን ለመግዛት ታቅዶ ወደ ሥራ መገባቱንም ገልጸዋል።

በመርሐ ግብሩ የተገኙት የብሔረሰብ አሥተዳደሩ ግብርና መምሪያ ኀላፊ ቤዛዊት ጌታሁን በተያዘው የምርት ዘመን ከ34 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት በበጋ መስኖ ስንዴ ለማልማት ታቅዶ የዘር ሥራ እየተከናወነ መኾኑን ተናግረዋል።

በበጋ መስኖ ከሚለማው ሰንዴ ከ1 ነጥብ 3 ሚሊዮን ኩንታል በላይ ምርት እንደሚጠበቅ ያነሱት ኀላፊዋ ይህንን ለማሳካት የሚያስችል በቂ ምርጥ ዘር እና ማዳበሪያ ለአርሶ አደሮች መቅረቡን ገልጸዋል።

የቀበሌው አርሶ አደሮችም ስንዴን በኩታገጠም ማልማት ከጀመሩ ወዲህ የተሻለ ተጠቃሚ መኾናቸውን ተናግረዋል።

በዚህ ዓመትም ስንዴን በመስኖ በማልማት ከራሳቸው ፍጆታ አልፎ ገበያውን ለመመገብ እየሠሩ መኾናቸውን ነው ያነሱት።

የኩታ ገጠም አመራረት ዘዴ ለተሻለ የውኃ አጠቃቀም፣ ተሞክሮ ለመለዋወጥ እና ለሰብል እንክብካቤ ምቹ ሁኔታ እንደፈጠረላቸውም አርሶ አደሮቹ ገልጸዋል።

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleየ13ሺህ ሥራ ፈላጊዎች ተስፋ ምን ላይ ነው?
Next article“እያንዳንዱ የሰላም ስምምነት የጥይት ድምፅ የማይሰማባት አሕጉር የመገንባት ግባችን ላይ ለመድረስ ያግዘናል” ምክትል ሊቀመንበር ሰልማ ማሊካ አዳዲ