የ13ሺህ ሥራ ፈላጊዎች ተስፋ ምን ላይ ነው?

22

ባሕር ዳር፡ ኅዳር 25/2018ዓ.ም (አሚኮ) የባሕር ዳር ልዩ የኢኮኖሚ ዞን በሀገረቱ ካሉ 10 ልዩ የኢኮኖሚ ዞኖች መካከል አንዱ ነው፡፡ ይህ ልዩ የኢኮኖሚ ዞን የኢንዱስትሪ ፓርክ በሚል ነበር በ2012 ዓ.ም ሥራ የጀመረው። ቅርብ በሚባል ጊዜ ደግሞ በርካታ ማሻሻያዎች እና ለውጦች ተደርገውበት ወደ ልዩ የኢኮኖሚ ዞን ተሸጋግሯል።

አኩሪ አተርን በመጠቀም ድፍድፍ ዘይት ማምረት ላይ የተሠማራው ፋብሪካ ሥራ አሥኪያጅ ራድሂሽያም ኪአር ልዩ የኢኮኖሚ ዞኑ በርካታ መሠረተ ልማቶች የተሟሉለት ነው ይላሉ። ነገር ግን በአቅራቢያ የሚገኝ ሥራ የጀመረ ደረቅ ወደብ ባለመኖሩ ምርቶቹን ወደ ውጭ ለመላክ የሚያስፈልግ ኮንቲነር ችግር እንደኾነባቸውም አንስተዋል።

ከአዲስ አበባ አካባቢ አስመጥቶ ለመጠቀም በሚደረግ አማራጭ እንቅስቃሴም ለከፍተኛ ወጭ እንደተዳረጉም ተናግረዋል። በጸጥታ ችግሩ ምክንያት ከአርሶ አደሮች የሚቀርቡ ግብዓቶች ላይ የዋጋ ጭማሪ እና የምርት እጥረት መኖር ሌላው ያጋጠማቸው ችግር መኾኑን ጠቅሰው ችግሩ እንዲፈታላቸው ጠይቀዋል።

የኤሌክትሪክ ትራንስፈርመር በማምረት እና በመጠገን ተግባር ላይ የተሠማራው ፋብሪካ ሥራ አሥኪያጅ ጌታቸው ቀለም ወርቅ ደግሞ ልዩ የኢኮኖሚ ዞኑ ደኅንነቱ የተጠበቀ እና ሁሉም መሠረተ ልማቶች የተሟሉለት በመኾኑ ውጤታማ ሥራ እየሠራን ነው ብለዋል።

ፋብሪካው የተለያየ መጠን ያላቸው አዲስ ትራንስፈርመሮችን የሚያመርት በክልሉ የሚገኝ ብቸኛ ተቋም መኾኑንም ተናግረዋል። ለኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት እና ለተለያዩ ድርጅቶች ምርቶችን እያቀረበ እንደሚገኝም ጠቅሰዋል። የሚመረተው ትራንስፈርመር የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት ያስቀመጠውን ደረጃ ያሟላ ጥራት ያለው መኾኑን አንስተዋል። ዋጋውም ተመጣጣኝ ነው ብለዋል።

ጥሬ እቃ ከሀገር ውጭ የሚመጣ ከመሆኑ ጋር ተያይዞ የትራንስፖርት እና የውጭ ምንዛሬ ችግር እየገጠማቸው መኾኑን ተናግረዋል። እንደ ሀገር የኤሌክትሪክ ትራንስፈርመር እጥረት እና ውስንነት ቢኖርም ያለው የገበያ ትስስር ግን ውስን መኾኑን አንስተዋል።

ከልዩ ዞኑ ሸድ በሊዝ ተከራይተው እየሠሩ እንደኾነ የገለጹት ሥራ አሥኪያጁ የኪራይ ዋጋ መሻሻሉን ጠቅሰው የክልሉ መንግሥት ከኪራይ የሚታደግ የመሥሪያ ቦታ እንዲያመቻችላቸው ጠይቀዋል።

በባሕር ዳር ልዩ የኢኮኖሚ ዞን ከፍተኛ የአይሲቲ ባለሙያ በመኾን እየሠሩ የሚገኙት አበባው ልዑለቃል ደግሞ ልዩ የኢኮኖሚ ዞኑ የሥራ ዕድል ከመፍጠር ባሻገር የቴክኖሎጅ ዕውቀት ሽግግር ላይ ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንዳለው ተናግረዋል።

ጊዜአዊ እና ቋሚ የሥራ ዕድል ከመፍጠር አኳያም ፋይዳው ከፍተኛ ቢኾንም በክልሉ የተፈጠረው የጸጥታ ችግር ባለሃብቶችን በሙሉ አቅም እንዳይሠሩ ስለሚያደርግ የሥራ ዕድል ፈጠራ ላይ ውስንነት እንዲኖር ማድረጉን ገልጸዋል።

የባሕርዳር ልዩ የኢኮኖሚ ዞን ሥራ አሥኪያጅ ጥሩየ ቁሜ ልዩ የኢኮኖሚ ዞኑ ኢትዮጵያ ለምታደርገው የኢኮኖሚ ሽግግር እንደ ድልድይ ኹኖ በማገልገል ረገድ ትልቅ ፋይዳ እንዳለው ተናግረዋል።

ለውጭ ሀገር ገብያ የሚቀርቡ ምርቶችን እና ከሀገር ውጭ ወደ ሀገር ውስጥ የሚገቡ ተኪ ምርቶችን በማምረት ከፍተኛ፣ መካከለኛ እና ዝቅተኛ ኢንዱስትሪዎች እንዲተሳሰሩ ለማድረግም ከፍተኛ ድርሻ እንዳለው ገልጸዋል።

የሥራ ዕድል ከመፍጠር እና የቴክኖሎጅ ሽግግር ከማምጣት አኳያም ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንዳለው አንስተዋል። የባሕር ዳር ልዩ የኢኮኖሚ ዞን አሁን ላይ ስምንት ሸዶች አሉት ያሉት ሥራ አሥኪያጇ ልዩ የኢኮኖሚ ዞኑ ይዟቸው የመጣቸው ዕድሎች እና ፀጋዎች መኖራቸውንም ጠቅሰዋል። ከእነዚህም ውስጥ፦

👉ኢንዱስትሪ ፓርክ በነበረበት ጊዜ በተወሰኑ የኢንቨስትመንት አማራጮች ማለትም በጨርቃ ጨርቅ ላይ ያተኮረው አሠራር አሁን ላይ የአግሮ ፕሮሰስ፣ የማኑፋክቸር እና ሌሎች አማራጮች መፍጠር መቻሉ

👉ቀደም ሲል የውጭ ሀገር ባለሃብቶችን ያበረታታ የነበረው አሠራር የውጭ ሀገር ባለሃብቶችን ሳያገል የሀገር ውስጥ ባለሃብቶችን የበለጠ ማበረታታቱ

👉ዝቅተኛ፣ መካከለኛ እና ከፍተኛ ባለሃብቶችን በትስስር እንዲሠሩ የሚያደርግ አሠራር መኖሩ

👉በተሟላ ሁኔታ አገልግሎት የሚሰጥ የአንድ ማዕከልን መሠረት ያደረገ የተሟላ መሠረተ ልማት መኖሩ።

ለአብነትም ስምንት ሜጋ ዋት የኤሌክትሪክ መብራት አቅርቦት እና ጄኔሬተር፣ ከ3ሺህ በላይ ሜትር ኪዩቭ ውኃ መያዝ የሚችሉ ሦሥት ጥልቅ የውኃ ጉድጓዶች፣ የፍሳሽ ማጣሪያ ግንባታ፣ የጽዳት እና የአረንጓዴ ልማት አገልግሎት፣ የተደራጀ የእሳት አደጋ ብርጌድ እና ሁለት የእሳት አደጋ አንቡላንስ፣ የመንገድ መሠረተ ልማት፣ ዳታ ሴንተር፣ በቴክኖለጅ የበለጸገ እና የተለያዩ አገልግሎቶች የሚሰጥ መኾኑ

👉 ለባለሀብቱ የእፎይታ ጊዜ እንዲኖረው መደረጉ

👉ከለማ መሬት እና ከሸድ የሊዝ ክፍያ ጋር ተያይዞ በባለሃብቶች ይነሳ የነበረ ጥያቄ ላይ ቅናሽ መደረጉ እና የቅድሚያ እና ሙሉ ክፍያ የሚያጠናቅቁበት ጊዜ መሻሻሉ

👉በባለሃብት ያልተያዙ ሦስት ሸዶች መኖር

👉 21 ሄክታር የለማ መሬት መኖርን በአብነት አንስተዋል።

በባሕርዳር ልዩ የኢኮኖሚ ዞን ሦሥት አይነት ዘርፎች ላይ ትኩረት ያደረጉ ፋብሪካዎች መኖራቸውን የተናገሩት የባሕርዳር ልዩ የኢኮኖሚ ዞን ሥራ አሥኪያጅ ጥሩየ ቁሜ ፋብሪካው

👉 እንደ ሀገር ብሎም በአማራ ክልል ያለውን የትራንስፈርመር እጥረት በመቀነስ በኩል አስተዋጽኦ ያለው የኤሌክትሪክ ትራንስፈርመር ማምረት እና መጠገን ሥራ ላይ የተሰማራ ፋብሪካ ስለመኾኑ ጠቁመዋል

👉 ጨርቃ ጨርቅ ማምረት ላይ የተሰማሩ ፋብሪካዎች እንዳሉትም አብራርተዋል።

👉ቀደም ሲል ከሀገር ውጭ ይመጣ የነበረውን የዘይት ድፍድፍ የሚተካ አኩሪ አተርን በመጠቀም የድፍድፍ ዘይት የሚያመርት እና ለውጭ ሀገር ገበያ የሚያቀርብ ፋብሪካ እና

👉በቆሎን በመጠቀም የስታርች ምግቦችን በማምረት ለሀገር ውስጥ ገብያ የሚያቀርብ ፋብሪካ በውስጡ እንደያዘም ጠቅሰውልናል።

ሁሉም ፋብሪካዎች ምርቶቻቸውን ወደ ውጭ ሀገር የመላክ እና ከውጭ ሀገር የሚመጡ ምርቶችን በሀገር ውስጥ ምርቶች በመተካት ላይ ትኩረት አድርገው እየሠሩ መሆኑንም ተናግረዋል።

ልዩ የኢኮኖሚ ዞኑ በሙሉ አቅሙ ወደ ሥራ ሲገባ ቁጥራቸው 13ሺህ ለሚደርሱ ሥራ ፈላጊዎች የሥራ ዕድል ይፈጥራል ነው ያሉት።

አሁን ባለው ተጨባጭ ሁኔታ ግን ሁሉም ሸዶች በሙሉ አቅማቸው ወደ ሥራ ካለመግባታቸው ጋር ተያይዞ የተፈጠረው የሥራ ዕድል ውስን እንደኾነ ተናግረዋል።

የአካባቢው አርሶ አደሮች የሚያመርቷቸውን የግብርና ምርቶች በግብዓትነት የመጠቀም እና የገበያ ትስስር የመፍጠር ሁኔታ እንዳለም አንስተዋል።

ባለሃብቶች የሚያነሱት አብዛኛው ጥያቄ የተመለሰ ቢኾንም ከኮንቲነር እና ሌሎች ጉዳዮች ጋር የተነሱ ጥያቄዎችን ለመፍታት ከክልሉ መንግሥት ጋር እየተወያዩ መኾኑን አስገንዝበዋል።

ውብ በኾነችው ባሕርዳር ከተማ ውብ መሠረተ ልማት የተሟላለት ልዩ የኢኮኖሚ ዞን ስላለ ባለሃብቶች ወደ ከተማዋ መጥተው እንዲያለሙ እና እነሱ ተጠቅመው ማኅበረሰብ እና ሀገርን ተጠቃሚ እንዲያደርጉም ጥሪ አስተላልፈዋል።

ዘጋቢ፦ ሮዛ የሻነህ

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን

Previous articleጥያቄው በጦርነት የተፈታለት ማኅበረሰብ የለም።
Next articleየመስኖ ምርታማነትን ለማሳደግ ቴክኖሎጂዎችን ጥቅም ላይ ለማዋል እየተሠራ ነው።