
ባሕር ዳር፡ ኅዳር 25/2018 ዓ.ም (አሚኮ) የሰላም ዋጋ ተመን የለውም፡፡ ተመን የሌለው ሰላም በአማራ ክልል ፈተና ከገጠመው ከሁለት ዓመታት በላይ ተቆጥሯል።
ለአማራ ክልል ከፍተኛ እና መካከለኛ መሪዎች “በመደመር መንግሥት ዕይታ፣ የዘርፎች እመርታ” በሚል መሪ መልዕክት ሥልጠና ተሰጥቷል። በሥልጠናው የተሳፉ መሪዎችም ሰላምን ማጽናት እንደሚገባ ተናግረዋል።
የወልድያ ከተማ አሥተዳደር የንግድ እና ገብያ ልማት መምሪያ ኀላፊ አዲሱ ወንድሙ በአማራ ክልል የተፈጠረው የጸጥታ ችግር እና አለመግባባት ቀኝ እጅ ከግራ እጅ ጋር እንደመጣላት ነው ብለዋል። አሁን ላይ በክልሉ አንጻራዊ ሰላም መፈጠሩንም ተናግረዋል።
የሥራ ኀላፊዎች አሁን የተፈጠረውን አንጻራዊ ሰላም ዘላቂ ለማድረግ እና የተጀመሩ የልማት ሥራዎችን ለማጠናቀቅ ቁርጠኛ መሪ መኾን እንደሚገባቸው ተናግረዋል። በክልሉ ከሚገኝ የጸጥታ መዋቅር ጋር መሥራት ይጠበቅብናልም ብለዋል።
የሥራ ኀላፊዎች ለሰላም እንቅፋት እየኾነ ያለውን አገልግሎት አሰጣጥ መፍታት እንደሚጠበቅባቸውም ተናግረዋል። የአማራ ክልል ሕዝብ የራሱ የኾኑ የባሕላዊ እርቅ እና የሽምግልና እሴት አለው ያሉት ኀላፊው እሴቶችን በመጠቀም ሰላምን ማረጋገጥ እንደሚገባ አመላክተዋል።
“የትኛውም ዓለም ላይ ጥያቄው በጦርነት የተፈታለት ማኅበረሰብ የለም”፤ አለመግባባቶች እና የጸጥታ ችግሩ በውይይት እና ድርድር ሊፈታ ይገባል ብለዋል።
በዋግኽምራ ብሔረሰብ አሥተዳደር ወፍላ ወረዳ ብልጽግና ፓርቲ ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት የፖለቲካ ዘርፍ ኀላፊ ዳርጌ ግደይ ደግሞ በክልሉ ባለው የጸጥታ ሁኔት እና በተደጋጋሚ በሚያደርገው ትንኮሳ ሕዝባችን አሁንም የተረጋጋ ሰላም አላገኘም ነው ያሉት። የማንነት እና የወሰን ጥያቄ ያለበት ኮረም እና አካባቢው ሰላም እንዲረጋገጥ እና ጥያቄው እንዲፈታ በተስፋ እየጠበቀ ነው ብለዋል።
ጦርነት ኪሳራ እንጅ ትርፍ የለውም ያሉት አቶ ዳርጌ አለመግባባቶች በንግግር ሊፈቱ ይገባል፤ የሰላም ችግር ማኅበረሰባችን እየጎዳው ነው ብለዋል። በኮረም አካባቢ በተደጋጋሚ የሚያደርገውን ትንኮሳም በቃ ማለት ይገባል ነው ያሉት።
ኢትዮጵያን ወደ ኋላ የሚጎትታት ጦረኝነት እና ብሔርተኝነት መኾኑንም ተናግረዋል። አስተሳሰብን ማስፋት ላይ ሰፊ ሥራ መሥራት ይጠይቃል ብለዋል።
በጸጥታ ችግር ውስጥ ተሁኖም በክልሉ በርካታ ተግባራት ተከናውነዋል፤ ሙሉ ሰላም ሲኖር ደግሞ የበለጠ ልማትን ማልማት ይቻላል ነው ያሉት።
የሥራ ኀላፊዎች እና የጸጥታ አካላት ከሕዝብ ጋር በመኾን ለሰላም መሥራት ይጠበቅብናል ነው ያሉት።
ዘጋቢ፦ ሮዛ የሻነህ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
