
ደብረ ብርሃን: ኅዳር 25/2018 ዓ.ም (አሚኮ) በዓለም ለ22ኛ ጊዜ በኢትዮጵያ ደግሞ ለ21ኛ ጊዜ የሚከበረው የጸረ-ሙስና ቀን “ትውልድን በሥነ ምግባር ተቋምን በአሠራር” በሚል መሪ መልዕክት በደብረ ብርሃን ከተማ ተከብሯል።
በመርሐ ግብሩ ላይ የደብረ ብርሃን ከተማ አሥዳደር እና የሰሜን ሸዋ ዞን የሥራ ኀላፊዎች እና ባለሙያዎች ተገኝተዋል። ሙስናን የመከላከል ተግባሩን ግንዛቤ ከመፍጠር ጀምሮ የሥነ ምግባር ግንባታ፣ በአስቸኳይ ሙስናን መከላከልን፣ የሃብት ምዝገባን፣ ትክክለኛነትን የማጣራት እና የማረጋገጥ ተግባር እየተከናወነ እንደሚገኝ የተናገሩት የአማራ ክልል ሥነ ምግባር እና ጸረ ሙስና ኮሚሽን የደብረ ብርሃን ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት ኀላፊ ረታ አሰግደው ናቸው።
ባለፈው በጀት ዓመት በተሠሩ ሙስናን የመከላከል ሥራዎች ከ2 ሚሊዮን ብር በላይ ማስመለስ ተችሏል ነው ያሉት። 37 የመንግሥት ተሿሚዎች እና ተመራጭ የመንግሥት ሠራተኞች ላይ ሃብት የማረጋገጥ ሥራ መከናወኑን ገልጸዋል።
ሙስናን ለመከላከል በተሠራው ሥራ የጽሑፍ ማስጠንቀቂያ እና ለተጨማሪ ምርመራ የተላኩ ግለሰቦች መኖራቸውንም ጠቁመዋል። ይህንን ተግባር በማጠናከር በ2018 በጀት ዓመት “የሕዝብ እና የመንግሥትን ሃብት ከምዝበራ ለመታደግ በትኩረት ይሠራል” ብለዋል።
በደብረ ብርሃን ከተማ አሥተዳደር ሙስና እና ብልሹ አሠራሮችን ለመታገል ዘመናዊ የመረጃ አያያዝ ሥርዓት ተግባራዊ መደረጉን የተናገሩት ደግሞ የከተማ አሥተዳደሩ ምክትል ከንቲባ ወርቃለማሁ ኮስትሬ ናቸው።
ይሁን እንጅ ታማኝነትን መሠረት ያደረገ እና በመርህ ላይ የተመሠረተ አገልግሎትን መስጠት አስፈላጊ ነው ብለዋል።
የሰሜን ሸዋ ዞን አሥተዳደር ምክትል አሥተዳዳሪ ተክለየስ በለጠ ትውልዱ ሙስናን በመጸየፍ በሥነ ምግባር እንዲታነጽ እና የሕግ የበላይነት እንዲረጋገጥ መሠራት አለበት ነው ያሉት። ለተግባራዊነቱም የዞኑ አሥተዳደር ይሠራል ብለዋል።
ዘጋቢ፦ ገንዘብ ታደሰ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
