
ባሕር ዳር: ኅዳር 25/2018 ዓ.ም (አሚኮ) ከፍተኛ የሥራ ኀላፊዎች በምሥራቅ ጎጃም ዞን በየደረጃው ከሚገኙ የሥራ ኀላፊዎች ጋር በደጀን ከተማ ተወያይተዋል።
በውይይቱ በምክትል ርእሰ መሥተዳድር ማዕረግ የአሥተዳደር ዘርፍ አስተባባሪ አማኑኤል ፈረደ (ዶ.ር)፣ የምሥራቅ ጎጃም ዞን አሥተዳዳሪ ኑርልኝ ብርሃኑ፣ በአካባቢው የሚንቀሳቀሰው የሀገር መከላከያ ሠራዊት ዕዝ አዛዥ ሜጄር ጄኔራል ብርሃኑ ጥላሁንን ጨምሮ ሌሎች ከፍተኛ የሥራ ኀላፊዎች ተገኝተዋል።
በቅንጅት በተሠራው ሥራ በዞኑ አንጻራዊ ሰላም መፍጠር መቻሉ ተገልጿል። በተደረጉ ተደጋጋሚ ውይይቶች በታጣቂ ቡድኑ ተደናግሮ የነበረውን ማኅበረሰብ ግንዛቤ ማስጨበጥ መቻሉም ተመላክቷል።
ዘላቂ ሰላምን ለማረጋገጥ የግንዛቤ ማስጨበጫ ውይይቶችን አጠናክሮ ማስቀጠል እና ታጣቂ ቡድኑን ከማኅበረሰቡ መነጠል ይገባል ተብሏል።
የሕግ ማስከበር ሥራውን ውጤታማ ለማድረግ ኀይል ማሰባሰብ፣ ማሠልጠን፣ ማደራጀት እና ማሠማራት ይገባል ነው የተባለው። በዞኑ የሰላም አስከባሪ እና የሚሊሻ አባላት እየሠለጠኑ ሕግ የማስከበር ሥራ እየሠሩ መኾናቸው ተመላክቷል።
የውይይቱ ተሳታፊዎች የሀገር መከላከያ ሠራዊት አካባቢው ወደ አንጻራዊ ሰላም እንዲመለስ ላደረገው አስተዋጽኦ ምስጋና ይገባዋል ብለዋል። መልማት የሚያስችሉ ጸጋዎች አሉ፤ በአንጻሩ ደግሞ ጸጋዎችን ለመጠቀም የጸጥታ ችግር አለ፤ ፈተናዎችን ወደ እድል በመቀየር እና ችግሮችን በመፍታት ጸጋዎችን እንጠቀማለን ነው ያሉት።
ዘላቂ ሰላምን ማረጋገጥ ዋናው ጉዳይ መኾኑን ተናግረዋል። ታጣቂ ቡድኑ የሚንቀሳቀስባቸውን ቀበሌዎች ነጻ በማውጣት ወደ ልማት ሥራዎች መሸጋገር እንደሚገባም አንስተዋል። ሰላምን እያረጋገጡ ተቋርጦ የቆየውን ትምህርት ለማስቀጠል እንደሚሠሩም ተናግረዋል።
እየተዳከመ የመጣውን ታጣቂ ቡድን በፍጥነት በማጽዳት ዘላቂ ሰላምን ማረጋገጥ ያስፈልጋል ነው ያሉት። በየቀኑ የሰላም አማራጭን የሚቀበሉ፣ አካባቢውን እየለቀቁ የሚሸሹ ታጣቂዎች መኖራቸውንም አንስተዋል።
የምሥራቅ ጎጃም ዞን አሥተዳዳሪ ኑርልኝ ብርሃኑ ከችግር የመውጫው ትልቁ ኀይል ሕዝብ ነው ብለዋል። ሕዝብን ከመደናገር እና ከስጋት ማውጣት እንደሚገባ ተናግረዋል። መሪዎች የግንዛቤ ፈጠራ ሥራዎችን እንዲሠሩ እና ታጣቂ ቡድኑን ከሕዝብ እንዲነጥሉ አሳስበዋል።
ታጣቂ ቡድኑ የሚንቀሳቀስባቸውን ቀበሌዎች እያጸዱ ወደ መደበኛ እንቅስቃሴ መግባት እንደሚገባ ተናግረዋል። የጸጥታ ችግሩን እንደ ምክንያት ተጠቅመው ወደ ሥራ ያልገቡ ባለሙያዎችን በተሟላ ሁኔታ ወደ ሥራ ማስገባት እንደሚጠበቅ ገልጸዋል።
ዘላቂ ሰላምን ለማረጋገጥ እስካሁን ከመጣንበት መንገድ በተለየ መንገድ መራመድ አለብን ነው ያሉት። ሕዝቡ ከዘራፊ እና ቀማኛ ቡድን አውጡኝ እያለ እየጠየቀ ነው፤ በፍጥነት ልንደርስለት ይገባል ብለዋል። እስካሁን ከነበረው ፍጥነት በመጨመር እና የአፈጻጸም ልሕቀት በማምጣት ሕዝብን መታደግ ያስፈልጋል ነው ያሉት።
በትብብር እና በአንድነት ሕዝብን ከችግር ማውጣት እንደሚያስፈልግም ተናግረዋል። በምክትል ርእሰ መሥተዳድር ማዕረግ የአሥተዳደር ዘርፍ አስተባባሪ አማኑኤል ፈረደ (ዶ.ር) በተከፈለ መስዋዕትነት ወደ አንጻራዊ ሰላም መሸጋገር መቻሉን ተናግረዋል። ነገር ግን መንግሥት እና ሕዝብ ከሚፈልጉት አንጻር የሚቀሩ ሥራዎች አሉ ነው ያሉት። ምሥራቅ ጎጃም ባለው ታላቅ አቅም ልክ እንዲለማ፣ ተጽዕኖ እንዲፈጥር እና ተወዳዳሪ እንዲኾን በቁርጠኝነት መሥራት ይጠበቅባችኋል ብለዋል።
በዞኑ ያለውን የትምህርት ችግር በፍጥነት መፍታት እና ትውልድን መገንባት እንደሚገባ ተናግረዋል። እየተወሰዱ ባሉ የሕግ ማስከበር እርምጃዎች ታጣቂ ቡድኑ እየፈራረሰ ነው ብለዋል። በየቀኑ የሰላም አማራጭን እየተቀበሉ የሚገቡትም በርካቶች መኾናቸውን ተናግረዋል። መንግሥት ያስቀመጣቸውን የልማት ዕቅዶችን ማሳካት እንደሚገባቸውም አሳስበዋል።
የጸጥታ ኀይሎችን በማጠናከር የሕግ ማስከበር ሥራውን አጠናክሮ መቀጠል እንደሚገባ አመላክተዋል። ታጣቂ ቡድኑ ባለበት ቦታ እየተከታተሉ እርምጃ መውሰድ እንደሚገባም ተናግረዋል። የሰላም አማራጭን እንዲቀበልም ግፊት ማድረግ ይጠበቃል ነው ያሉት።
ቀበሌዎችን ለልማት የተመቹ ማድረግ እንደሚያስፈልግም ተናግረዋል። መሪዎች የመልካም አሥተዳደር እና የአገልግሎት አሰጣጥ ችግርን መፍታት እንደሚገባም አመላክተዋል። በትብብር በመሥራት ወደ መደበኛ ሰላም መመለስ ያስፈልጋል፤ ሰላምን በማረጋገጥ የሕዝብን ተጠቃሚነት ማረጋገጥ ይጠበቃል ነው ያሉት። የእያንዳንዱን አካባቢ ሰላም በማረጋገጥ በክልሉ የተሟላ ሰላም መፍጠር እንደሚገባም ተናግረዋል።
ዘጋቢ:- ታርቆ ክንዴ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን
