
ባሕር ዳር: ኅዳር 25/2018 ዓ.ም (አሚኮ) የአማራ ወጣቶች አረንጓዴ ፎረም ባለፉት ዓመታት ባከናወናቸው እና በቀጣይ በሚያከናውናቸው ተግባራት ዙሪያ ምክክር አድርጓል። ፎረሙ ሕጋዊ እውቅና ካገኘ ጀምሮ በችግኝ ተከላ፣ በከተሞች ውበት እና ጽዳት ላይ እየተሳተፈ ይገኛል።
የፎረሙ አባል የኾነው ቴዎድሮስ አደራጀው የወጣቶች አረንጓዴ ፎረም ባለፉት ዓመታት በተለያዩ የልማት ሥራዎች ላይ በመሳተፍ የድርሻውን መወጣቱን ገልጸዋል። በቀጣይም በሀገሪቱ እየተሠሩ በሚገኙ የአረንጓዴ ልማት ሥራዎች ላይ ከመሳተፍ ባለፈ የተሠሩ ሥራዎችን ለሌሎች ሀገራት የማስተዋወቅ ሥራ እንደሚሠሩም ገልጸዋል።
ደኅንነቷ የተጠበቀ ሀገርን ለመጭው ትውልድ ለማስረከብ ወጣቶች ለአረንጓዴ ልማት ትኩረት እንዲሰጡ ጠይቀዋል። የአማራ ወጣቶች አረንጓዴ ፎረም ፕሬዝዳንት በለጠ ወዳጅነው ፎረሙ ባለፉት ዓመታት በሠራው ሥራ የወጣቱን የመደራጀት አቅም አሳይቷል፤ በችግኝ ተከላ በተለይ ደግሞ በአረንጓዴ አሻራ መርሐ ግብር ከተጀመረ ጀምሮ ወጣቶችን በማሳተፍ ፎረሙ ትልቅ ሥራ ሠርቷል ብለዋል።
የተሠሩ ሥራዎችንም የማስተዋወቅ ሥራ መሠራቱን ነው የገለጹት። በከተሞች የኮሪደር ልማት ላይ ወጣቶችን በማሳተፍ ፎረሙ የድርሻውን ተወጥቷል ብለዋል። ልማት እና ሰላም የማይነጣጠሉ እንደመኾናቸው ወጣቶች ከአረንጓዴ ልማት ባለፈ ሰላም ላይ እንዲሳተፉ መደረጉንም ገልጸዋል።
አረንጓዴ ልማት ዓለም አቀፍ አጀንዳ እንደመኾኑ በቀጣይ አረንጓዴ ዲፕሎማሲ እና አረንጓዴ ሽልማት ላይ ትኩረት ተደርጎ የሚሠራባቸው ሥራዎች መኾናቸውን ነው የገለጹት። ፎረሙ አማራ ክልል ላይ መቀመጫውን ቢያደርግም ሌሎች የክልሉ ወጣቶችን ያካተተ የአብሮነት ማሳያ መኾኑ ተናግረዋል።
የአማራ ክልል ሴቶች፣ ወጣቶች እና ማኅበራዊ ጉዳይ ቢሮ ምክትል ኀላፊ ዘላለም አረጋ የሀገር አንድነት እና እድገት መሠረት የኾነውን ወጣት ክፍል ማደራጀት የሀገርን ልማት እና ሰላም ማፋጠን ነው ብለዋል።
ወጣቶች ከአረንጓዴ ልማት ባለፈ በሁለንተናዊ ልማት ላይ እንዲሳተፉ የተደራጀ ድጋፍ እንደሚደረግ ገልጸዋል። “ወጣቶች መልካም እሴቶችን እና ባሕሎችን በመጠበቅ የችግሮች የመፍትሔ አካል እንዲኾኑም” አሳስበዋል።
ዘጋቢ: ዳግማዊ ተሠራ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
