
ደብረ ብርሃን: ኅዳር 25/2018 ዓ.ም(አሚኮ) የሰሜን ሸዋ ዞን እና የደብረ ብርሃን ከተማ አሥተዳደር የሃይማኖት ተቋማት የሰላም ኮንፈረንስ አካሂደዋል።
በመድረኩ ላይ የደብረ ብርሃን ከተማ ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ በድሉ ውብሸት የሰላም እጦት በክልሉ ማኅበራዊ ፖለቲካዊ እና ኢኮኖሚያዊ ችግሮችን አስከትሏል ብለዋል። ለዚህ የሰላም እጦት መስተካከል የሃይማኖት አባቶች እና የሀገር ሽማግሌዎች አስተዋጽኦ ከፍተኛ መኾኑንም ተናግረዋል፡፡
በተለይም እንደ ኢትዮጵያ አማኝ ሕዝብ ባለባት ሀገር የሃይማኖት ተቋማትን እና የባሕላዊ እሴቶችን በመጠቀም የሀገርን ሰላም ለማስፈን መሥራት ይገባል ነው ያሉት።
የአማራ ክልል የሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ ጽሕፈት ቤት ኀላፊ ፋሲል ታዬ ሰላም በረከት ብቻ ሳይኾን የሁላችንም የሞራል ኀላፊነት ነው ብለዋል፡፡ እውነተኛ ሰላም ከራስ ይመነጫል፤ ወደ ቤተሰብ እና ወደ ሀገርም የሚሰፋ ሃብት ነው ያሉት ኀላፊው ሰላምን መምረጥ በፈጣሪም የተወደደ ተግባር ነው ብለዋል።
በክልሉ ላለው ሰላም ሥራ በክልሉ የተካሄደው የሰላም ኮንፈረንስ ውጤት አምጥቷል ነው ያሉት። ለውይይት ለይቅርታ እና ለሰላም ሁላችንም ቁርጠኛ ከኾን የምንሻውን ሰላም ማምጣት እንችላለን ብለዋል።
ተሳታፊ የሃይማኖት መሪዎች የሰላም እጦቱ ምን ያህል እንደጎዳን የተረዳነው አሁን ነው ብለዋል። “የሰላም ዋጋውን በአግባቡ የምንረዳው ሰላም ባጣን ሰዓት ነው” ያሉት የሃይማኖታዊ አባቶቹ ትዕዛዛትን ብንከተል እና ብናከብር አሁን የገጠመን አይነት ችግር ባልገጠመን ነበር ነው ያሉት፡፡ መሪዎቹ አሁንም ቢኾን ለማስተካከል አልረፈደም ሲሉ ተናግረዋል።
ዘጋቢ:- ለዓለም ለይኩን
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
