ሰላም እንዲሰፍን ሁሉም የድርሻውን ሊወጣ እንደሚገባ የሃይማኖት አባቶች አሳሰቡ።

4

ጎንደር: ኅዳር 25/2018 ዓ.ም (አሚኮ) የማዕከላዊ ጎንደር ዞን እና የጎንደር ከተማ የሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ “ሃይማኖት የሰላም መሠረት ነው” በሚል መሪ መልዕክት የሰላም ጥሪ ሰልፍ አካሂደዋል። በሰልፉ የሃይማኖት አባቶች እና የጎንደር ከተማ ነዋሪዎች ተገኝተዋል።

የማዕከላዊ ጎንደር ሀገረ ስብከት ሥራ አስኪያጅ ሊቀ ሥልጣናት አባ ዮሴፍ ደስታ የሰልፉ ዓላማ የሰላም እጦቱ ያሳደረውን ጫና በመገንዘብ ሁሉም ለሰላም እጁን እንዲዘረጋ ለማሳሰብ ነው ብለዋል። በጦርነት እና በአፈሙዝ የሚፈታ ነገር የለም ያሉት አባ ዮሴፍ ለሰላም እጅን መዘርጋት ያስፈልጋል ነው ያሉት።

የድህነት ምንጩ ግጭት ነው ያሉት አባ ዮሴፍ ሰላምን ማስቀደም አስፈላጊ መኾኑን በአንክሮ ተናግረዋል። በግጭት ምክንያት ተማሪዎች ወደ ትምህርት ገበታ እንዳይመጡ፣ ሕዝቡ ደስታ እና በሀዘን እንዳይገናኝ እንቅፋት አድርጓል ያሉት ሊቀ ሥልጣናት ወደ ልቦናችን ተመልሰን ሰላምን እናስቀድም ብለዋል።

አምላክ የሚወደው የሰላምን መንገድ ስንከተል ነው ያሉት አባ ዮሴፍ ጥያቄዎች በንግግር እንዲፈቱ ወደ ውይይት መምጣት ያስፈልጋል ነው ያሉት። የጎንደር ከተማ አሥተዳደር ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ ቻላቸው ዳኘው የታጠቁ ኃይሎች ከደም አፋሳሽ ተግባር በመራቅ ወደ ሰላም እንዲመጡ መልዕክት አስተላልፈዋል።

የጎንደር ዑለማ እና የእስልምና ምክር ቤት ሰብሳቢ ሼህ ሀጅ ኢብራሒም ሙሐመድ የሰላም እጦት የሰው ልጆችን ብቻ ሳይኾን ፍጥረታትን ሁሉ የሚያጠፋ ነው ብለዋል። ሰላም ከሌለ የእምነት ሥርዓትን መከወን፣ ከቦታ ቦታ መንቀሳቀስ አይቻልም ነው ያሉት።

የሰላም እጦት ሴቶች እንዲደፈሩ፣ አዛውንቶች እንዲገደሉ እና የኑሮ ውድነት እንዲከሰት እያደረገ ይገኛል ያሉ ሼህ ሀጅ ኢብራሒም ሰላምን ማስፈን እና ማጽናት ያስፈልገናል ብለዋል። የኢትዮጵያ ካቶሊካዊት ቤተ ክርስቲያን አገልጋይ አማኑኤል በየነ ሰላም የሚጀምረው ከሰው ልጅ ልብ በመኾኑ ከልባችን በመነሳት ሰላም እውን ማድረግ እንደሚገባ አንስተዋል።

የአማራ ክልል የሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ አባል መልዓከ ብርሃን ፍስሐ ጥላሁን የገጠመን የእርስ በርስ ግጭት እገታ፣ ዝርፊያ እና ግድያን አስከትሏል፣ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ተማሪዎች ከትምህርት ገበታ እንዲርቁ እና የሰው ልጅ ሕይዎት እንዲጠፋ አድርጓል ብለዋል።

በመኾኑም በውይይት እና በንግግር በማመን ነባር እሴቶቻችንን ልናስቀጥል እና ሰላምን ልናጸና ያስፈልጋል ነው ያሉት። በጫካ ውስጥ ያሉ አካላት የሕዝቡን ችግር በመረዳት ወደ ሰላም እንዲመጡም ጥሪ አቅርበዋል።

የኢትዮጵያ የሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ የቦርድ አባል መምህር ዳንኤል ሰይፈ ሚካኤል በማኅበራዊ ሚዲያ የሚደረጉ የጥላቻ ንግግሮችን እና ግጭት ቀስቃሽ ድርጊቶችን ልናወግዝ ይገባል ብለዋል።

መንግሥት ለዘርፉ ትኩረት በመስጠት የማኅበራዊ ሚዲያ ቁጥጥር ሊያደርግ እንደሚገባም አሳስበዋል።

በሀገራችን የሚታዩ ግጭቶች በሰላማዊ ሁኔታ እንዲፈቱ የሃይማኖት አባቶች እና ሕዝቡ የበኩሉን ድርሻ እንዲወጣም ጥሪ አቅርበዋል።

ዘጋቢ:- ያየህ ፈንቴ

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleየጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ(ዶ.ር) መልዕክት፦
Next article“የሰላም ዋጋውን በአግባቡ የምንረዳው ሰላም ባጣን ሰዓት ነው” የሃይማኖት መሪዎች።