
ባሕር ዳር: ኅዳር 24/2018 ዓ.ም (አሚኮ) የባሕር በር ቀጣናዊ የጆኦ ፖለቲካ የበላይነትን ለመቆጣጠር የሀገራት የደም ሥር ተደርጎ ይወሰዳል። በተለይም ደግሞ ቀይ ባሕር የሜዲትራኒያን እና የሕንድ ውቅያኖስን የሚያስተሳስር በመኾኑ ከጥንት ጀምሮ በአውሮፓ፣ በእስያ እና በአፍሪካ የተነሱ ኃያላን መንግሥታትን ትኩረት የሚስብ ኾኖ ከሺህ ዓመታት በላይ መዝለቁን ያዕቆብ ኃይለማርያም (ዶ.ር) “የኢትዮጵያ የባሕር በር ጥያቄ” በሚል ካሳተሙት መጽሐፋቸው ላይ አስፍረውት ይገኛል።
የፋርስ ጦረኞች፣ የዓረብ ነጋዴዎች፣ ታላቁ እስክንድር እና መሰል በየዘመናቱ የተነሱ ኃያላን መንግሥታት እና ሀገር አሳሾች የዚህን መስመር ወሳኝ ስትራቴጂካዊ ጠቀሜታ መስክረውለታል፡፡ ሌላው ቀርቶ በየዘመናቱ የተነሱ የባሕር ጃዊሳዎች መስመሩን መተላለፊያቸው ለማድረግ ሲሽቀዳደሙ ኖረዋል ይላል መረጃው፡፡
ቀይ ባሕር ቅኝ ግዛትን ለማስፋፋት እና ቀጣናውን ለመቆጣጠር ጥንታዊ ግሪኮች፣ ጥንታዊ ሮማውያን፣ ጥንታዊ ሕንዶች እና ቻይናዎች፣ ቱርኮች፣ ግብጾች፣ ጣሊያን፣ እንግሊዝ፣ ፈረንሳይ እና ኢትዮጵያን ጨምሮ የበርካታ ሀገራት መናህሪያ እና የጦር ሠራዊት መተላለፊያ ኾኖም አገልግሏል ሲሉ ዶክተር ያዕቆብ በመጽሐፋቸው አትተዋል።
አካባቢው ካለው ስትራቴጅካዊ ጠቀሜታ አኳያ የአሸባሪዎች ኢላማ ለመኾን የተመቼ በመኾኑ ኃያላን ሀገራት ጭምር በአካባቢው ላይ የጦር ሰፈር እስከ ማቋቋም ደርሰዋል ሲሉ ነው ያተቱት። በእንጅባራ ዩኒቨርሲቲ የፖለቲካል ፍልስፍና መምህር አለምነህ አጋዥ ቀይ ባሕር ከጥንት ጀምሮ እስከ አሁን ኃያላን ሀገራት ዐይናቸውን ከጣሉባቸው ቀጣናዎች ዋነኛው ነው ይላሉ።
ሀገራት የራሳቸውን የጦር ሰፈር የመሠረቱበት እና ለመመሥረት እየሠሩ እንደሚገኙም ተናግረዋል። በዚህ አካባቢ እንደ ሳዑዲ አረብያ፣ ኢራን፣ የተባበሩት ዓረብ ኢምሬትስ፣ ኳታር፣ እስራኤል፣ ቱርክ እና የመሳሰሉ በቀጣናው ቅርብ ርቀት ላይ የሚገኙ ሀገራት ወታደራዊ ሰፈሮችን በመገንባት ኃይላቸውን የሚያሳዩበት ቀጣና ኾኗል ነው ያሉት፡፡
አሜሪካ፣ የአውሮፓ ሀገራት፣ ሩስያ፣ ቻይና፣ ጃፓን እና የመሳሰሉ በርቀት የሚገኙ ሀገራትም ጭምር በቀይ ባሕር ላይ ከሚንቀሳቀሱ ሀገራት ውስጥ ተጠቃሾች ናቸው ብለዋል፡፡ አሜሪካ ብቻ በአረብ ባሕረ ሰላጤ እና በምሥራቅ አፍሪካ አካባቢ ላይ እየተንሰራፋ የመጣውን የአሸባሪዎች እንቅስቃሴ ለመቆጣጠር በየጊዜው በድሮን እና በሳተላይት ጭምር የታገዘ ክትትል ታደርጋለች ነው ያሉት።
በቅርቡም በቀጣናው የሰላም እና ደኅንነት ላይ ከኢትዮጵያ ጋር በጋራ ለመሥራት ውይይቶችን ማድረጋቸው የዚህ አንዱ ማሳያ ተደርጎ ሊወሰድ ይችላል ብለዋል። ቻይናም በአካባቢው ወታደራዊ የጦር ሰፈር አቋቁማ በ10 ሺህ የሚጠጋ ሠራዊት አስፍራለች ነው ያሉት፡፡ ጃፓን እና ፈረንሳይም ወታደራዊ ሰፈር ካቋቋሙ ሀገራት ይጠቀሳሉ ብለዋል። ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ደግሞ ሳዑዲ አረብያ” የየመን ሁቲዎችን ለመውጋት” በሚል ሰበብ በጂቡቲ ወታደራዊ ካምፕ ለመመስረት ውል ተፈራርማለች።
ይህ በቀጣናው ላይ የሚታየው የኃያላን እና የአካባቢው ሀገራት ወታደራዊ ፉክክር ምን አንድምታ ሊኖረው ይችላል? የሚለው ጥያቄ በቀላሉ ሊታይ የሚችል እንዳልኾነ ያሳያል ነው ያሉት። በአንጻሩ ከ120 ሚሊዮን በላይ ሕዝብ ያላት ኢትዮጵያ ደግሞ በአንዳንድ የምዕራብ እና የመካከለኛው ምሥራቅ ሀገሮች ሴራ ከ30 ዓመት በላይ ከታሪካዊ ይዞታዋ እንድትገለል ተደርጎ ቆይቷል ብለዋል መምህሩ። በዚህም ምክንያት በአካባቢው የነበራትን ተሰሚነት እና ክብር እንዲቀንስ ማድረጉን ነው መምህሩ የገለጹት።
ኢትዮጵያ አሁን ላይ በቀጣናው ካላት የሕዝብ ቁጥር፣ የመልከዓ ምድራዊ አቀማመጥ፣ ለባሕር በር ካላት ቅርበት አኳያ እና በቀጣናው እየጨመረ ከመጣው የሀገራት ፉክክር አኳያ የራሷን ብሎም የቀጠናውን ደኅንነት ለማስጠበቅ በቀይ ባሕር ላይ ዋነኛ ተዋናይ ኾና መውጣት የሕልውና ጉዳይ መኾኑን ገልጸዋል።
ለዚህ ደግሞ ጥያቄውን በሕጋዊ መንገድ እንዲፈታ ቅድሚያ ሰጥቶ መሥራት ይገባል ብለዋል። እ.ኤ.አ በ1982 በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የወጣው ኮንቬንሽን የዓለም ሀገራት የባሕር ክልል እና ወሰንን በምን መንገድ መጠቀም እንዳለባቸው መሠረታዊ መርሆዎችን አስቀምጧል። ይህንንም 169 የዓለም ሀገራት ፈርመውበታል ብለዋል።
ሕጉ ዓለም አቀፍ የውኃ ክልል አጠቃቀምን እንዲሁም በባሕር ወሰን የሚነሱ ውዝግቦች እና የችግር አፈታት ሂደቶችን በዝርዝር አስቀምጧል። ከውኃማ አካላት ጋር የማይገናኙ ዝግ ሀገራት በዙሪያቸው ከሚገኙ የባሕር በር ካላቸው ሀገራት አገልግሎት የሚያገኙበት መብት እንዳላቸው በኮንቬንሽኑ ላይ መቀመጡን ነው የገለጹት።
የአጠቃቀሙ ጉዳይ በሁለቱ ሀገራት ስምምነት ጭምር የሚወሰን ይኾናል። እ.ኤ.አ 2005 ሞልዶቫ ከዩክሬን ጋር ባደረገችው ሥምምነት ዓለም አቀፍ የውኃ መዳረሻ በኾነው የዳንዩብ ወንዝ አካባቢ መሬት በስምምነት ተቀብላ እየተጠቀመች እንደሚገኝ በማሳያነት አንስተዋል።
ኢትዮጵያ የባሕር በር ባለቤት መኾኗ ምን ዕድሎችን ይዞ ይመጣል? የባሕር በር የንግድ እና የትራንስፖርት ወጭን እንዲቀንስ ያደርጋል፤ የወጭ እና ገቢ ለውውጥን ለማፋጠን ፋይዳው የጎላ ነው። የውጭ ኢንቨስትመንት ይስባል፤ ከወደብ አገልግሎት ገቢ ለመፍጠር ያስችላል፤ ብሔራዊ ሥልጣን እና ነጻነትን ያጎናጽፋል፤ ከጎረቤት ሀገራት ጥገኝነትን ያላቅቃል፤ የክልላዊ ተጽዕኖ ፈጣሪነትን እና ተሰሚነትን ያሳድጋል፤ የባሕር ሃብቶችን ለመጠቀም ምቹ ሁነታ ይፈጥራል ነው ያሉት።
ለበርካታ ወጣቶችም የሥራ ዕድል የመፍጠር አቅም አለው ብለዋል። ከውጭ የሚገቡ ሸቀጦች ዋጋ ይቀንሳል፣ በባሕር እና በሎጀስቲክስ ዘርፍ የሰው ኃይል ለማልማት ያግዛል። የባሕር በር ጥያቄ ቀጣናዊ የዲኦ ፖለቲካዊ የበላይነትን ለማረጋገጥ፣ ከድኅነት ለመውጣት፣ የወጭ እና የገቢ ንግድን ለማሳለጥ ወሳኝ ጉዳይ መኾኑንም አንስተዋል።
የባሕር በር ጥያቄው በሌሎች ሀገራት ጭምር ይበልጥ ድጋፍ እንዲያገኝ የዲፕሎማሲ ሥራውን አጠናክራ መሥራት ያስፈልጋል ነው ያሉት መምህሩ። ምሁራን እና ፖለቲከኞች ጥያቄው የሕልውና ጉዳይ መኾኑን ተረድተው ለሀገራቸው ዲፕሎማት ኾነው ሊሠሩ ይገባል ብለዋል።
ኢትዮጵያውያን ግድቡን በመተባበር እንደፈጸሙት ኢትዮጵያ ታሪካዊ የባሕር በር ተጠቃሚነቷ እንዲረጋገጥም ማኅበረሰቡ የዜጋ ዲፕሎማትነቱን ሊወጣ ይገባል ብለዋል።
በዳግማዊ ተሠራ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
