
ባሕር ዳር፡ ሰኔ 15/2012 ዓ.ም (አብመድ) የአፍሪካ ቀንድ ቀጣና ጂኦፖለቲካ ስሪት በገንጣይ አስገንጣይ ጋብቻ ላይ የተመሠረተ ነው፡፡ ከሐሳብ የተናጠበ፣ ምክንየተዊነት የጎደለው፣ ነገን ከመመልከት ይልቅ ትናንት ላይ የተቸከለ እና ሴራ የጥበቡ መልህቅ የሆነ ይመስለል፡፡ የወቅቱ የቀጣናው ዓበይት ጉዳይ ደግሞ ታላቁ የኢትዮጵያ የሕዳሴ ግድብ ግንባታ ነው፡፡ አጀንዳው ከስምምነት እስከ ውይይት፣ ከድርድር እስከ ክርክር እንዲሁም ከማመልከቻ እስከ ማስፈራሪያና ዛቻ ሞቅ፣ ቀዝቀዝ ሲል ይስተዋላል፡፡
በዓባይ ወንዝ ላይ ለዘመናት የተጎነጎኑት ሴራዎች የተፋሰሱ ሀገራት ብቻ ሳይሆኑ የወራሪዎችም የእርስ በርስ የጥቅም ግጭት ምንጭ ነበሩ፡፡ ይህ ደግሞ ዛሬም ድረስ እንደቀጠለ ነው፡፡ በወቅቱ ፈረንሳይ የግብፅ እንደራሴ የነበረችውን እንግሊዝን ለማስወጣት ኢትዮጵያ ጋር ግንኙነት ጀመረች፡፡ የመሰልጠን ጉጉት የመዘመን ፍላጎት እንዳላቸው ልብ ያሏቸውን ምኒልክን ከጂቡቲ እስከ አዲስ አበባ የባቡር መንገድ ሠርተው ተወዳጇቸው፡፡ ቀጥለውም በጣና ሐይቅ ላይ ግድብ እንዲሠሩ አግባቧቸው፡፡ የጣና ሐይቅ ግድብ የአካባቢው የፖለቲካ መዘውር መሆኑን ያስተዋለችው እንግሊዝም አራት ኪሎ ቤተ መንግሥት ድረስ ዘልቃ ቢያንስ እስከ ንጉሠ ነገሠቱ ሞት የግንባታው ጉዳይ የሚራዘምበትን ዕፎይታ አገኘች፡፡
በጣና ሐይቅ ላይ ግድብ መሥራት የሚለው ሐሳብ የግብፅን እና የሱዳንን ትኩረት ሳበ፡፡ ሐሳቡ እንደ ሐሳብ እስከ አንደኛው የዓለም ጦርነት መጀመር ቢቆይም ጦርነቱ በተለኮሰ በዓመቱ በ1915 (እ.አ.አ) የሦስቱ ሀገራት የጋራ ኮሚሽን የጣና ሐይቅን ጎበኘ፡፡ ፍላጎቱ ምን እንደሆነ ቢታወቅም በ1924 (እ.አ.አ) ራስ ተፈሪ መኮንን ለንደንን እስከሚጎበኙበት ጊዜ ድረስ ጎልቶ የወጣ ሐሳብ አልነበረም፡፡ በወቅቱ በእንግሊዝ መንግሥት በኩል ጥያቄው የተነሳላቸው ራስ ተፈሪም ቅጭም ያለ መልስ ሰጧቸው “ግድቡ የሚሠራም ከሆነ ግድቡን የምትሠራው ኢትዮጵያ እንጂ ሌላ ማንም አይሆንም” ሲሉ፡፡
እንግሊዝ እና ፈረንሳይ ኢትዮጵያ ሳታውቅ ሊሠሩት ያሰቡት ግድብ ዘግይቶም ቢሆን ከንጉሡ ጆሮ ደረሰ፡፡ ንጉሡ ጉዳዩን ለሊግ ኦፍ ኔሽን ካቀረቡ በኋላም ሁለቱ ሀገራት እጃቸውን እንዲሰበሰቡ ቀጠን ያለች ትዕዛዝ አስተላለፉ፡፡ ከንገሡ በኋላ የምኒልክን ቤተ መንግሥት የተቀበሉት ፕሬዝዳንት መንግሥቱ ኃይለማሪያምም ቢሆን ዓባይን ለመገደብ ያልጣሩበት ጊዜ አልነበረም፡፡ የግብፅ ሴራ እና ድህነት እግር ከወርች አስሮ ሕልማቸውን እውን ባያደርጉም፡፡
ጊዜ ሲሰጥ ድህነት ባይጠፋም እልህ እና ወኔ ዓባይን ከሦስት መንግሥታት ጥረት እና ውጣ ውረድ በኋላ ለመገደብ ተጀመረ፡፡ ያም ሆኖ ግን ነገሮች አልጋ ባልጋ አልነበሩም፡፡ እስከዚህ ዘመን የደረሰ ውጥረት እና ሙግትን አስከትሏል፡፡ የተፈጠረውን መልካም አጋጣሚ በአግባቡ አለመጠቀምም ዋጋ አስከፍሏል፡፡
የሰሞኑ የቴክኒክ ጉዳይ እና እንድምታውስ ምን ይመስላል?
ከሰሞኑ ግብፅ፣ ሱዳን እና ኢትዮጵያ እያደረጉት ያለው ድርድር ቴክኒካል ጉዳዮች ላይ ያተኮረ ነው ያሉት የተደራዳሪው ቡድን አባል እና የቴክኒክ ኮሚቴ ጽሕፈት ቤት ዋና ሥራ አስኪያጅ ፈቅ አህመድ ‘‘ግብፅ ግን ድርድሩን ከቴክኒካል ጉዳዮች ይልቅ ፖለቲካዊ እና ዲፕሎማሲያዊ ለማድረግ ስትጥር ይስተዋላል’’ ነው ያሉት፡፡ ከወትሮውም ቢሆን የቴክኒክ አደራዳሪዎቿን ከሁለቱ ሀገራት ጋር አስቀምጣ ከአሜሪካ እስከ ፀጥታው ምክር ቤት ጉዳዩን ለምታሯሩጠው ግብፅ የቴክኒክ ውይይቱ ላይ የዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ተፅዕኖ ጎትቶ እንዳስገባት ግልፅ ነው፡፡
ግንባታው ከተጀመረበት ጊዜ አንስቶ ኢትዮጵያ ለውይይት እና ለምክክር በሯን ክፍት ያላደረገችበት ጊዜ አለመኖሩንም አስታውሰዋል፡፡ ውይይቱ በግብፅ ተለዋዋጭ አቋም ምክንያት ለውጥ አለማምጣቱንም ተናግረወል፡፡ ‘‘የተፋሰሱ የታችኞቹ ሀገራት በተለይም ግብፅ ቢቻላቸው ግድቡን ማስቆም ፍላጎታቸው ነው’’ ያሉት አቶ ፈቅ አሁን የሚያደርጉት እንቅስቃሴ ግድቡ ውኃ እንዳይዝ ለማድረግ የመጨረሻ አማራጭ እየተጠቀሙ እንደሆነም አስታውቀዋል፡፡
‘‘በግድቡ ግንባታ ሁለቱ ሀገራት ተጠቃሚ እንጂ ተጎጂ አለመሆናቸው በጥናት ጭምር ተደግፎ ቀርቧል’’ ያሉት ተደራዳሪው አቶ ፈቅ አማራጫቸው ነገሩን ሰከን ብለው ዓይተው ወደመተማመን እና ትብብር መምጣት እንደሆነ ይጠቁሟሉ፡፡ ከማይለወጠው የግብፅ ፍላጎት በስተጀርባ የማይቆም የኢትዮጵያውያን የመልማት ፍላጎት አለ፡፡
ዘጋቢ፡- ታዘብ አራጋው
ተጨማሪ መረጃዎችን
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
ትዊተር https://bit.ly/37m6a4m
ዩቱዩብ https://bit.ly/38mpvDC ያገኛሉ፡፡
