
ጎንደር: ኅዳር 24/2018 ዓ.ም (አሚኮ) የማዕከላዊ ጎንደር ዞን እና የጎንደር ከተማ የሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ “ሃይማኖት የሰላም መሠረት ነው” በሚል መልዕክት ከተለያዩ የኅብረተሰብ ክፍሎች ጋር ውይይት አካሂዷል።
በውይይቱም ከጎንደር ከተማ እና ከማዕከላዊ ጎንደር ዞን የተወጣጡ የኅብረተሰብ ክፍሎች ተገኝተዋል።
የውይይቱ ተሳታፊ አቶ አስረስ መሐመድ በጸሎት እና በውይይት ሰላም እንዲመጣ ልንሠራ ይገባል ብለዋል። የሀገርን አንድነት ለማጽናት ሰላም ወሳኝ በመኾኑ ለሰላም መጽናት የበኩላችንን መወጣት አለብን ነው ያሉት።
ሌላው የውይይቱ ተሳታፊ መልዓከ ኃይል ቆሞስ አባ ገብረ እግዚአብሔር አንድነት እና ፍቅርን ሊያመጣ የሚችለው ከቤተሰብ ጀምሮ ስለሰላም ማስተማር ሲቻል መኾኑን አንስተዋል።
መላከ ገነት ቆሞስ አባ ብርሃነ መስቀል ደርበው በሰላም እጦት አርሶ አደሮች ለከፋ ችግር እየተጋለጡ በመኾናቸው ወደ አርሶ አደሮች ቀርቦ ማወያየት እና ሰላም እንዲመጣ ማድረግ እንደሚያስፈልግ አንስተዋል።
የሃይማኖት አባቶች ጫካ የገቡ አካላትን ቀርቦ በማወያየት ከመንግሥት ጋር የሚወያዩበትን መንገድ ማመቻቸት እንደሚገባ ጠቅሰዋል።
ከተማ ላይ ብቻ ሳይኾን ገጠር ላይ በመሄድ እና በማወያየት መፍትሄ እንዲመጣ መሥራት ያስፈልጋል ያሉት ደግሞ የውይይቱ ተሳታፊ የሀገር ሽማግሌ አቶ ገብሬ ሞገስ ናቸው።
ሌላኛው የውይይቱ ተሳታፊ የሀገር ሽማግሌ አቶ ምኅረት ጓል የትራንስፖርት ችግር፣ የኑሮ ውድነት፣ የሰላም እጦት ለሕዝቡ ፈተና እና አስቸጋሪ እንዳደረገው ገልጸዋል።
ሰላም እንዲመጣ እና ማኅበረሰቡ የዕለት ተግባራትን ያለ ስጋት እንዲከወን ለሰላም መሥራት አለብን ብለዋል።
የኢትዮጵያ የሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ የቦርድ አባል መምህር ዳንኤል ሰይፈ ሚካኤል ሥልጣኔ፣ እድገት እና ታሪክ የሚኖሩት ሰላም ሲኖር በመኾኑ ለአብሮነት እና ሰላም በትጋት እንደ አባትነት መሥራት እንደሚያስፈልግ አብራርተዋል።
የአማራ ክልል የቅርስና ታሪክ ዘርፍ ተጠሪ እና የጎንደር ክላስተር አስተባባሪ አሕመዲን አብዱልቃድር ውይይቱ አንዱ ስለ ሌላው መኖርን እና መከባበርን ያየንበት ነው ብለዋል።
እሴቶቻችን ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተሸረሸሩ በመኾናቸው እሴቶቻችንን መጠበቅ እና ማሳደግ ያስፈልጋል ነው ያሉት።
የአማራ ክልል የሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ አባል መልዓከ ብርሃን ፍስሃ ጥላሁን የሃይማኖት አባቶች በሁሉም ቦታዎች በመገኘት ስለሰላም ማስተማር ያስፈልጋል ብለዋል።
ሁሉም በተሰጠው ጸጋ ልክ ዘላቂ ሰላም እንዲረጋገጥ ኀላፊነቱን ሊወጣ እንደሚገባ አሳስበዋል።
የማዕከላዊ ጎንደር ሀገረ ስብከት ሥራ አስኪያጅ ሊቀ ሥልጣናት አባ ዮሴፍ ደስታ እርስ በርስ በመከባበር እና በመደጋገፍ ሰላም እንዲጸና ልንሠራ ይገባል ብለዋል።
ዘጋቢ:- ያየህ ፈንቴ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
