የኅብረተሰቡን የንጹሕ መጠጥ ውኃ አቅርቦት ችግር ለመቅረፍ እየተሠራ ነው።

7
ጎንደር: ኅዳር 24/2018 ዓ.ም (አሚኮ) በማዕከላዊ ጎንደር ዞን ወገራ ወረዳ የአምባ ጊዮርጊስ ከተማ አሥተዳደር ነዋሪዎች በንጹሕ መጠጥ ውኃ ተደራሽነት እጥረት ምክንያት ለእንግልት እና ለጤና ችግር መዳረጋቸውን ተናግረዋል።
አሚኮ ያነጋገራቸው የከተማዋ ነዋሪ ቄስ መኳንንት ደሴ በመኖሪያ ቦታ አቅራቢያ ውኃ ማግኘት አለመቻላቸውን ገልጸውልናል። ውኃ ለማግኘት በሌሊት መጓዝን ጨምሮ በርካታ ሰዓታትን ወረፋ በመጠበቅ ለእንግልት መዳረጋቸውንም ነው የተናገሩት።
በንጹሕ መጠጥ ውኃ እጥረት በሕጻን ልጃቸው ላይ የጤና እክል እንደገጠማቸው ያነሱት ደግሞ ሌላኛዋ የከተማው ነዋሪ ወይዘሮ ረህመት ዳውድ ናቸው። ችግሩ የከተማዋን ነዋሪዎች እየፈተነ መኾኑንም ገልጸዋል።
የአምባ ጊዮርጊስ ከተማ አሥተዳደር መጠጥ ውኃ እና ፍሳሽ አገልግሎት ድርጅት ዋና ሥራ አስኪያጅ ሰጠኝ እንድሪስ በከተማዋ ከፍተኛ የንጹሕ መጠጥ ውኃ ተደራሽነት ችግር ያለ መኾኑን ገልጸዋል።
ችግሩን ለመፍታት የአማራ ክልል ውኃ እና ኢነርጂ ቢሮ የውኃ ሥርጭት እና መስመር ዝርጋታ ሥራ ቢጀምርም ተግባሩ ሙሉ ለሙሉ አለመጠናቀቁን ተናግረዋል።
አሁን ላይ የከተማዋ የውኃ ተደራሽነት ሽፋን 18 በመቶ መኾኑን ያነሱት ሥራ አስኪያጁ ሽፋኑን ወደ 72 በመቶ ለማሳደግ ታሳቢ ተደርጎ የተጀመረው ፕሮጀክት ከ65 ሚሊዮን ብር ወጭ ተደርጎበት ተጠናቅቆ መመረቁን አስታውሰዋል።
ከተመረቀ በኋላ ከቀናት ያለፈ አገልግሎት መስጠት ሳይችል አገልግሎት መስጠት ማቆሙን አመላክተዋል። ችግሩን ለመፍታት ጥረት እየተደረገ መኾኑንም ገልጸዋል።
የአምባ ጊዮርጊስ ከተማ አሥተዳደር ከንቲባ ተወካይ ዘነበ እንየው የኅብረተሰቡን ጥያቄ ለመፍታት ከሚመለከታቸው የክልሉ ባለድርሻ አካላት ጋር እየተሠራ መኾኑን በማስረዳት ችግሩ በቅርብ ጊዜ እንደሚፈታም አረጋግጠዋል።
ዘጋቢ:- ቃልኪዳን ኃይሌ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
Previous articleስለ ሰላም በአንድነት እንነሳ።
Next article“ደብረ ብርሃን ከተማ የአልሚዎችን ቀልብ እየሳበች ነው” አፈ ጉባኤ ፋንቱ ተስፋዬ