ስለ ሰላም በአንድነት እንነሳ።

6
ባሕር ዳር: ኅዳር 24/2018 ዓ.ም (አሚኮ) ከፍተኛ የሥራ ኀላፊዎች በምሥራቅ ጎጃም ዞን ከብቸና ከተማ አሥተዳደር እና ከእነማይ ወረዳ ነዋሪዎች ጋር በወቅታዊ ሁኔታዎች ላይ ተወያይተዋል።
በውይይቱ በምክትል ርእሰ መሥተዳድር ማዕረግ የአሥተዳደር ዘርፍ አሥተባባሪ አማኑኤል ፈረደ (ዶ.ር)፣ የምሥራቅ ጎጃም ዞን አሥተዳዳሪ ኑርልኝ ብርሃኑ፣ በአካባቢው የሚንቀሳቀሰው የሀገር መከላከያ አዛዥ ሜጄር ጄኔራል ብርሃኑ ጥላሁን እና ሌሎች ከፍተኛ የሥራ ኀላፊዎች ተገኝተዋል።
የውይይቱ ተሳታፊዎች የተፈጠረው የጸጥታ ችግር ለከፋ ችግር ዳርጎናል፤ በየቀኑ እንጀራ አውጡ፣ ገንዘብ አምጡ መባል ሰልችቶናል ብለዋል።
ሰዎች እየታገቱ ገንዘብ እየተጠየቀባቸው ነው፣ እውነትን የተናገርን እንደኾነ እየታፈን ነው፣ ከዚህ በላይ በዚህ መከራ ውስጥ መኖር ይበቃናል፣ እናግዛችሁ አካባቢውን ሰላም አድርጉልን ነው ያሉት።
የሃይማኖት አባቶች እና የሀገር ሽማግሌዎች እየመከሩ መመለስ አለባቸው ብለዋል። ክፉ ነገርን የሚያወግዝ፣ መልካም ነገርን የሚያስተምር አባት እንደሚያስፈልግም ተናግረዋል።
ከልባችን ተነስተን በቃን ልንል ይገባል ነው ያሉት። በነጻነት ተንቀሳቅሶ መኖር እንዳልተቻለም ተናግረዋል።
ልጆቻችን ከትምህርት ገበታ ውጭ ኾነዋል፤ ትውልድ እየመከነ ነው፣ በአጭር ጊዜ ውስጥ ከግጭት መውጣት ይገባል ነው ያሉት።
መንግሥት እያደረገ ያለው የሰላም ጥሪ የሚደነቅ ነው፣ አሁንም ተጠናክሮ መቀጠል አለበት፤ የሰላም አማራጭን በማይቀበሉት ላይ ግን ተከታትሎ እርምጃ መውሰድ አለበት ብለዋል።
መረጃ የሚያቀብሉ፣ ግጭቱ እንዲራዘም የሚፈልጉ እና በሁለት ቢላ የሚበሉ አካላትን ተከታትሎ እርምጃ መውሰድ እንደሚገባም አንስተዋል።
አካባቢው የተትረፈረፈ ጸጋ እያለው በሰላም እጦት ምክንያት መልማት አልቻልንም ብለዋል። ሰላምን የምንጠብቀው ራሳችን ነን፣ ከሰላም የምናተርፈውም እኛው ነን፣ ስለ ሰላም በአንድነት እንነሳ ነው ያሉት።
ሁሉም በየሚናው ስለ ሰላም መሥራት አለበት፣ ፖለቲካውን ለፖለቲከኞች ብቻ መስጠት ተገቢ ነው ብለዋል። ልማት የሚገኘው ሰላም ሲኖር ነው ያሉት ነዋሪዎቹ ሰላም ካልተረጋገጠ ልማት እንደማይመጣም ተናግረዋል። በተፈጠረው የጸጥታ ችግር ምክንያት ባለሃብቶች አካባቢውን እየለቀቁ መሰደዳቸውንም አንስተዋል።
ለአማራ ሕዝብ የተቆረቆረ ልጆቻችን ከትምህርት ገበታ አያስቀርም፤ ልጆቻችን እየሠረቀ ብር አይቀበልም፤ ገንዘብ ካልሰጣችሁኝ ብሎ አይገድም ነው ያሉት። ለሕዝብ የሚያስብ እንዳንቀሳቀስ አያደርግም፣ ለሕዝብ የሚያስብ ንብረታችን አይዘርፍም፤ ይህ ቡድን ለእኛ አይጠቅምም በአንድነት ተነስተን ራሳችን ማስከበር አለብን ብለዋል።
በጫካ የወጣው ቡድን ዓላማ መዝረፍ እና ሃብት መሰብሰብ ብቻ ነው፤ ለዚህ ደግሞ በየቀኑ ከምንዘረፈው እና ሃብት አምጡ ከምንባለው በላይ ምስክር የለም ነው ያሉት።
የሰላም አማራጭን የማይቀበሉት ሃብት እየሰበሰቡ ስለኾነ ነው ብለዋል። የሃይማኖት አባቶችን የሚገድል እና የሚያዋርድ ቡድን እንደማይጠቅምም ተናግረዋል።
ወላዶች ወደ ጤና ተቋም ሄደው እንዳይወልዱ የሚያደርግ ቡድን እንደማይጠቅምም ተናግረዋል። ኢትዮጵያ እየጠየቀች ያለውን የባሕር በር ጥያቄ እንድታገኝ እና ሌሎች የተጀመሩ ታላላቅ ፕሮጄክቶች እንዲሠሩ የውስጥ አንድነትን ማጠናከር እና ሰላምን ማረጋገጥ ይገባል ነው ያሉት።
ከሁሉም አስቀድሞ ሰላማችን ይከበርልን፤ የምንፈልገው ሰላም ነው፣ ሌላው ተከታይ ነው ብለዋል። ሰላም አልሰጠን ያለው በውስጣችን የተሰገሰገው ነው፣ ይሄን በአንድነት ማጥራት አለብን ነው ያሉት። መንግሥት የተጠናከረ እርምጃ እንዲወስድም ጠይቀዋል። የጸጥታ ችግሩን እንደ መልካም አጋጣሚ በመጠቀም የኑሮ ውድነትን የሚያባብሱ አካላት መኖራቸውንም ተናግረዋል።
ሁሉም የሃይማኖት አባቶች ሃይማኖቱ የሚያዝዘውን ማድረግ አለባቸው፣ ሃይማኖትን በማይመጥን ተግባር መሳተፍ የለባቸውም፤ ትውልዱም እውነተኛ የሃይማኖት አባቶች የሚሉትን መቀበል አለበት ነው ያሉት።
የምሥራቅ ጎጃም ዞን አሥተዳዳሪ ኑርልኝ ብርሃኑ ግጭት ከጉስቁልና አላወጣንም፣ ከጉስቁልና የሚያወጣው ሰላምን ማረጋገጥ ነው ብለዋል። ሁሉም ነገር ከሕዝብ የተሰወረ አይደለም ያሉት አሥተዳዳሪው ይበቃል ብላችሁ ከተነሳችሁ ሰላምን ማረጋገጥ ይቻላል ነው ያሉት።
ቀን ሰላማዊ የሚመስል፣ ማታ ደግሞ ገዳይና አስገዳይ፣ ዘራፊ እና አዘራፊ አለ ይሄን ማጋለጥ ከኅብረተሰቡ ይጠበቃል ብለዋል። ይሄ ሲኾን የአካባቢውን ሰላም ዘላቂ እና አስተማማኝ ማድረግ ይቻላል ነው ያሉት።
ሰላምን ማረጋገጥ ካልተቻለ ልማትን ማምጣት እንደማይቻልም ተናግረዋል። ሰማይ ቢቀደድ ሽማግሌ ይሰፋዋል በሚባልበት ማኅበረሰብ ውስጥ በግጭት መቆየት ተገቢ አይደለም፤ የሀገር ሽማግሌዎች እና የሃይማኖት አባቶች የራሳችሁን ድርሻ መወጣት አለባቸው ነው ያሉት። ለሰላም ሲባል የሚከፈለውን ዋጋ ሁሉ መክፈል እንደሚገባ ተናግረዋል።
ልማትን ለማረጋገጥ፣ የኑሮ ውድነትን ለመግታት ሰላምን ማረጋገጥ ያስፈልጋል ብለዋል። ያለ አግባብ ዋጋ የሚጨምሩትን፣ ምርት የሚደብቁትን እና ሕዝብ የሚያማርሩትን ጫካ ወጥተው ከሚዋጉት ነጥለን አናያቸውም፤ እርምጃ በመውሰድ እናስተካክላቸዋለን ነው ያሉት።
ግጭት እንዲባባስ የሚያደርጉ እና ሕዝብን የሚያደናግሩ አካላትን እንደማይታገሱም ገልጸዋል። ሕዝቡ በችግር ውስጥ ቆይቷል፣ መከራውን ሰምቶ ሳይኾን ደርሶበት አይቶታል፣ ይህን ሕዝብ ለዳግም መከራ የሚዳርጉ አካሄዶች ተቀባይነት የላቸውም ነው ያሉት። ዘላቂ ሰላምን ለማረጋገጥ በአንድነት መሥራት እንደሚገባም ተናግረዋል።
ከሕዝብ ጋር ኾነን ሰላምን እናረጋግጣለን፣ የልማት ጥያቄዎችንም እንመልሳለን ነው ያሉት። ለሰላም እና ለልማት በአንድነት እንዲቆሙም ጥሪ አቅርበዋል።
ዘጋቢ:- ታርቆ ክንዴ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
Previous articleባለኮከብ ሆቴሎችን ለመገንባት ቦታ የወሰዱ ባለሃብቶች በፍጥነት አጠናቅቀው አገልግሎት እንዲሠጡ ርእሰ መሥተዳድር አረጋ ከበደ አሳሰቡ።
Next articleየኅብረተሰቡን የንጹሕ መጠጥ ውኃ አቅርቦት ችግር ለመቅረፍ እየተሠራ ነው።