
ፍኖተ ሰላም: ኅዳር 24/2018 ዓ.ም (አሚኮ) የምዕራብ ጎጃም ዞን ሴቶች፣ ወጣቶች እና ማኅበራዊ ጉዳይ መምሪያ ከዞኑ አካል ጉዳተኞች ፌዴሬሽን ጋር በመተባበር በዓለም አቀፍ ደረጃ ለ34ኛ ጊዜ በሀገራችን ደግሞ ለ33ኛ ጊዜ የአካል ጉዳተኞችን ቀን አክብሯል።
”አካል ጉዳተኝነትን የሚያካትት ማኅበረሰብ መገንባት ለተሻለ ማኅበራዊ እድገት” በሚል መሪ መልዕክት ነው ቀኑ የተከበረው።
አስተያየታቸውን ለአሚኮ የሰጡ አካል ጉዳተኞች እንደተናገሩት ማኅበረሰቡ ለአካል ጉዳተኞች የሚሰጠው አመለካከት ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተሻሻለ መምጣቱን ገልጸዋል። የሚገነቡ መሠረተ ልማቶች አካል ጉዳተኞችን ታሳቢ ያደረጉ እንዲኾኑ በየወቅቱ መመሪያዎች ቢወጡም ተግባራዊ እየተደረጉ አለመኾናቸውንም አንስተዋል።
አካል ጉዳተኞች የትኛውንም ዓይነት ሥራዎች መሥራት የሚችሉ መኾናቸውን የሚገልጹት አስተያየት ሰጭዎቹ ለዚህም አስፈላጊ ግብዓቶችን ማሟላት እንደሚገባ ጠቁመዋል።
መንግሥትም በየጊዜው የሚያወጣቸውን መመሪያዎች ተግባራዊ በማድረግ ለአካል ጉዳተኞች ተጠቃሚነት ትኩረት እንዲሰጥ ጠይቀዋል።
የምዕራብ ጎጃም ዞን የአካል ጉዳተኞች ፌዴሬሽን ፕሬዝደንት ንጉሴ ምህረቴ የአካል ጉዳተኞችን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ ጥያቄዎችን ወደ ሚመለከተው አካል በማቅረብ ምላሽ እንዲያገኙ እየሠራ መኾኑን ተናግረዋል።
መንግሥት የአካል ጉዳተኞችን ሁለንተናዊ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ በርካታ የሕግ ማዕቀፎች ማውጣቱ የሚበረታታ መኾኑን ገልጸዋል። ይሁን እንጅ አሥፈጻሚ አካላት ለተግባራዊነቱ ተግዳሮት እየፈጠሩ ናቸው ብለዋል። ቀጣይ የሕግ ማዕቀፎችን ተፈጻሚ የማያደርጉ አካላትን ተጠያቂ ለማድረግ እንደሚሠራም አስረድተዋል።
አካል ጉዳተኞች ተጠቃሚነታቸውን ለማረጋገጥ እና ተሳትፏቸውን ለማሳደግ ከተለያዩ አካላት ጋር በጋራ እየሠሩ መኾናቸውን የተናገሩት ደግሞ የምዕራብ ጎጃም ዞን ሴቶች፣ ወጣቶች እና ማኅበራዊ ጉዳይ መምሪያ ኀላፊ ስለእናት ዘሪሁን ናቸው።
ከአጋር ድርጅቶች ጋር በመኾን እና ግብዓት በማሟላት አካል ጉዳተኞች በሁሉም ዘርፍ ውጤታማ እንዲኾኑ ሰፊ ሥራ እየተከናወነ ስለመኾኑም አስረድተዋል።
በበዓሉ ላይ የተገኙት የምዕራብ ጎጃም ዞን ብልጽግና ፓርቲ ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት የፖለቲካ እና አቅም ግንባታ ዘርፍ ኀላፊ ሙላት ጌታቸው አካል ጉዳተኝነት ሳይታሰብ በሰው ሠራሽ እና ተፈጥሯዊ ምክንያቶች ሊፈጠር የሚችል ክስተት መኾኑን ገልጸዋል።
አካል ጉዳተኞች ሌሎች የማኅበረሰብ ክፍሎች የሚሠሯቸውን ተግባራት መሥራት የሚችሉ እንደኾኑም አንስተዋል። በየትኛውም የአገልግሎት ዘርፎች ላይ አካል ጉዳተኞችን ታሳቢ ያደረጉ ተግባራትን መሥራት እንደሚገባ ነው የተናገሩት።
በዓሉን አስመልክቶ በፍኖተ ሰላም ከተማ ለሚገኙ አቅመ ደካሞች ማዕድ የማጋራት ሥራ ተከናውኗል።
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
