
ደብረ ብርሃን: ኅዳር 24/2018 ዓ.ም (አሚኮ) 20ኛው የብሔር፣ ብሔረሰቦች እና ሕዝቦች ቀን “ዴሞክራሲያዊ መግባባት ለኅብረ ብሔራዊ አንድነት” በሚል መሪ መልዕክት በአማራ ክልል ደረጃ የማጠቃለያ መርሐ ግብር በደብረ ብርሃን ከተማ ተከብሯል።
የደብረ ብርሃን ከተማ ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ በድሉ ውብሸት ደብረ ብርሃን ከተማ የሁሉም ብሔር ብሔረሰቦች መናኸሪያ ነች ብለዋል።
የከተማዋ ኢንቨስትመንት እድገት ዘላቂ፣ ፈጣን እና አስተማማኝ በኾነ መልኩ እየተረጋገጠ እንደሚገኝ ተናግረዋል
የአማራ ክልል ምክር ቤት አፈ ጉባኤ ፋንቱ ተስፋዬ 20ኛው የብሔር ብሔረሰቦች እና ሕዝቦች ቀን በዓል ከወረዳ ጀምሮ በልዩ ድምቀት ሲከበር ቆይቷል ብለዋል። የበዓሉ መከበር እርስ በርሳችን እንድንተዋወቅ አድርጎናል ነው ያሉት።
በአማራ ክልል ብሔር ብሔረሰቦች በጋራ በፍቅር እና በአንድነት ይኖራሉ ብለዋል። ይህም ኅብረ ብሔራዊ አንድነታችን የሕልውናችን መሰረት መኾኑን ገልጸዋል።
የእለቱ የክብር እንግዳ የፌዴሬሽን ምክር ቤት አፈ ጉባኤ አገኘሁ ተሻገር የብሔር፣ ብሔረሰቦች እና ሕዝቦች ቀንን ለማክበር ሲታሰብ ኅብረ ብሔራዊ አንድነት እንዲሰፍን በማሰብ ነው ብለዋል።
ይህም ሁሉም ብሔር፣ ብሔረሰቦች እና ሕዝቦች መብታቸው እንዲከበር እና ሀገራዊ መግባባት እንዲፈጠር አድርጓል ነው ያሉት።
የኢትዮጵያን ኅብረ ብሔራዊነት በልኩ ሊያሳይ በሚችል መልኩ በዓሉ እየተከበረ እንደሚገኝ ተናግረዋል።
የአማራ ክልል ከመነሻው ኅብረ ብሔራዊነት ማሳያ ነው፤ የተለያዩ ብሔር፣ ብሔረሰቦች በፍቅር የሚኖሩበት ነው ብለዋል።
በክልሉ ያጋጠመውን የሰላም እጦት ችግር ለመቀልበስ ከሚደረገው ጥረት ጎን ለጎን ልማት እንዲረጋገጥ የሚደረገው ጥረት አስደናቂነቱን አንስተዋል።
ወደ ጫካ የገቡ ኀይሎችን በቃችሁ ማለት ይገባል ያሉት አቶ አገኘሁ መንግሥት የሰጠውን የሰላም አማራጭ በመጠቀም አሉ የሚባሉ ጥያቄዎችን በሰላማዊ መንገድ ማቅረብ ወቅቱ የሚጠይቀው ተግባር መኾኑን አስረድተዋል።
ማኅበረሰቡም እንደተለመደው ሕግ ለማስከበር የሚደረጉ ጥረቶችን ሊደግፍ ይገባል ብለዋል።
በበዓሉ አከባበር ላይ የጨፌ ኦሮሚያ፣ የአፋር ክልል እና የአዲስ አበባ ከተማ አሥተዳደር አፈ ጉባኤዎች እና የአማራ ክልል ከፍተኛ የሥራ ኀላፊዎች ተገኝተዋል።
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
