የጉበት በሽታ መከላከያ ክትባት መሰጠት ተጀመረ።

6
ባሕር ዳር: ኅዳር 24/2018 ዓ.ም (አሚኮ) የአማራ ክልል ጤና ቢሮ የጉበት በሽታ (ሄፕታይተስ ቢ) የመከላከያ ክትባትን በባሕር ዳር ከተማ በይፋ አስጀምሯል።
በባሕር ዳር ጤና ጣቢያ የተወለደ ልጃቸውን ሲያስከትቡ ያገኘናቸው አቶ አዲሱ ንብረት ልጆቻቸው በጤና ተቋም እንደተወለዱ ገልጸዋል። የጉበት በሽታን እንደሚያውቁ እና ነገር ግን ክትባት መኖሩን እንደማያውቁ ነግረውናል።
ኅብረተሰቡም ግንዛቤው ኖሮት ሕጻናቶቹን እንዲያስከትብ ግልጽነት ሊፈጠርለት እንደሚገባ ነው አቶ አዲሱ የገለጹት።
የወንድማቸውን ልጅ ሲያስከትቡ ያገኘናቸው ወይዘሮ ትዕግስት ገበየሁ ደግሞ የክትባትን ጠቀሜታ እንደሚገነዘቡ ገልጸዋል። ልጆቻቸውንም አስከትበው እንዳሳደጉ ተናግረዋል። ነገር ግን ከዚህ ቀደም ለጉበት በሽታ ክትባት መኖሩን እንደማያውቁ ነው የጠቀሱት።
የባሕር ዳር ከተማ አሥተዳደር ጤና መምሪያ ምክትል ኀላፊ ጌትነት አባት የጤና ፖሊሲያችን መከላከል ላይ ያተኮረ ነው ይላሉ። የሕጻናትን ሞት ለመቀነስም ክትባት እየተሰጠ ነው ብለዋል።
በርካቶችን ለሞት እየዳረገ ያለው የጉበት በሽታ ገዳይነቱ ከፍተኛ እንደኾነ ነው የገለጹት። ለመከላከልም ከሕጻናት መጀመር ስላለበት በከተማ አሥተዳደሩ ለተወለዱ 14 ሺህ ህጻናት ክትባቱን ለመስጠት መታቀዱን ገልጸዋል።
ኅብረተሰቡ ክትባቱ በአዲስ መጀመሩን አውቆ ሕጻናቶቹን እንዲያስከትብም ጥሪ አስተላልፈዋል።
በአማራ ክልል ጤና ቢሮ የክትባት ፕሮግራሞች አማካሪ ወርቅነህ ማሞ የጉበት በሽታ ሄፒታይተስ ቢ በሚባል ቫይረስ የሚመጣ በሽታ ነው ብለዋል። ብዙ የኅብረተሰብ ክፍልም በበሽታው ይጠቃል ነው ያሉት።
ሕጻናትን እንደተወለዱ ክትባቱን በመስጠት ከእናት ወደ ልጅ እንዳይተላለፍ ማድረግ እንደሚቻልም ገልጸዋል። ህጻናት ከተቻለ እንደተወለዱ ወዲያውኑ ካልኾነም በ14 ቀናት ውስጥ መከተብ ያስፈልጋል ነው ያሉት።
የጉበት በሽታ ተላላፊ እና አደገኛ በሽታ ነው ያሉት አቶ ወርቅነህ በክትባት ለመከላከል በትኩረት እየተሠራ መኾኑን ገልጸዋል።
በሽታው በግብረ ሥጋ ግንኙነት እና በደም ንክኪ ይተላለፋል ብለዋል። በኢትዮጵያም ሰፊ ችግር እያስከተለ ነው፤ ከ800 ሺህ በላይ ሕጻናት ክትባቱን እንዲወስዱ ታቅዷልም ብለዋል።
የጉበት በሽታው ከእናት ወደ ልጅ ቢተላለፍ ወደ ካንሰርነት የመቀየር ዕድሉ ከፍተኛ ስለኾነ አስቀድሞ ለመከላከል ሕጻናትን የማስከተብን መፍትሔነት አመላክተዋል።
በሀገር አቀፍ ደረጃ ሰባት በመቶ የኾነው የኅብረተሰብ ክፍል እና አምስት በመቶ ነፍሰጡሮች በበሽታው እንደሚጠቁ መረጃዎች ያሳያሉ ብለዋል።
የአማራ ክልል ጤና ቢሮ ምክትል ኀላፊ አበበ ተምትሜ የጉበት በሽታ በሰፊው እየተሠራጨ መኾኑን ተናግረዋል። በሆስፒታል ከሚተኙ ህሙማን እና የሞት አደጋ ከሚያጋጥማቸው 35 በመቶ ያህሉ የጉበት በሽተኞች እንደኾኑም ገልጸዋል።
የጉበት በሽታን ጨምሮ በክትባት የምንከላከላቸው በሽታዎች 15 ደርሰዋል ያሉት ምክትል ቢሮ ኀላፊው ኅብረተሰቡም የክትባቱ ተጠቃሚ እንዲኾን አሳስበዋል።
ዘጋቢ: ዋሴ ባዬ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
Previous articleየሃይማኖት አባቶች የሰላም መልዕክተኞች በመኾናቸው ዘላቂ ሰላም እንዲመጣ በትኩረት ሊሠሩ ይገባል።
Next articleአካታች ማኅበረሰብ በመገንባት አካል ጉዳተኞችን በልዩ ልዩ ጉዳዮች ተሳታፊ ማድረግ ይገባል።