
ጎንደር: ኅዳር 24/2018 ዓ.ም (አሚኮ) የማዕከላዊ ጎንደር ዞን እና የጎንደር ከተማ የሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ “ሃይማኖት የሰላም መሠረት ነው” በሚል መሪ መልዕክት ከሃይማኖት አባቶች እና ከማዕከላዊ ጎንደር ዞን እና ጎንደር ከተማ አሥተዳደር ከተወጣጡ የኅብረተሰብ ክፍሎች ጋር የሰላም ውይይት በጎንደር ከተማ እያካሄዱ ነው።
በውይይቱ የማዕከላዊ ጎንደር ሀገረ ስብከት ሥራ አስኪያጅ ሊቀ ሥልጣናት አባ ዮሴፍ ደስታ ሰላም የሚመጣው በሁሉም ሰው ጥረት በመኾኑ ለሰላም ልንሠራ ይገባል ብለዋል። ከሰብዓዊነት መውጣት፣ መከፋፈል፣ አለመተማመን እና መነጣጠል የሰላም እጦትን አምጥቷል ብለዋል።
ተወያይተን የማንግባባ እና ተነጋግረን የማንተማመን በመኾናችን ሰላምን ከእጃችን አጥተናታል ብለዋል ሊቀ ሥልጣናት አባ ዮሴፍ። በሀገር እና አካባቢ የሰላም ተግባር ላይ መተማመን እና መደጋገፍ እንደሚገባ አባ ዮሴፍ አሳስበዋል።
የጎንደር ከተማ ዑለማ እና የእስልምና ምክር ቤት ሰብሳቢ ሼህ ሀጅ ኢብራሂም ሙሃመድ ሰላም ለሀገር እና ለሃይማኖት ወሳኝ በመኾኑ ሰላምን በቃል ሳይኾን በተግባር ልንገልጠው ይገባል ብለዋል።
የሰው ልጅ እየታገተ ገንዘብ ሊጠየቅ አይገባም ያሉት ሼህ ሀጅ ኢብራሂም በመተዛዘን፣ በመደጋገፍ እና ከሰብዓዊነት የወጣ ተግባርን በማራቅ ስለ ሰላም ልንሠራ ይገባልም ነው ያሉት።
ውይይቱ ሰላምን ለማጽናት የመፍትሔ አቅጣጫዎችን ለማስቀመጥ የተዘጋጀ መኾኑን ገልጸዋል። እንደ ሃይማኖት አባትነት ለሰላም የበኩላችንን ድርሻ ልንወጣ ይገባል ብለዋል።
በውይይቱ ላይ የተገኙት የአማራ ክልል የሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ አባል መልዓከ ብርሃን ፍስሃ ጥላሁን የሰላም እጦቱ በክልል ደረጃ ከፍተኛ ጫና ያደረሰ በመኾኑ የሃይማኖት አባቶች ሰላምን ለማጽናት በማስተማር እና በመምከር ሰላምን ልናመጣ ይገባል ብለዋል።
በጸሎት፣ በውይይት እና በተግባር ሰላም እንዲመጣ፣ በድርድር እና ውይይት ግጭቶች እንዲፈቱ መሥራት ይገባናልም ነው ያሉት።
የጎንደር ከተማ አሥተዳደር ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ ቻላቸው ዳኘው ጎንደርን የከተሞች እናት ብለን ስንጠራ የአብሮነት ከተማ በመኾኗ ነው ብለዋል። የሃይማኖት አባቶች በከተማዋ አንጻራዊ ሰላም እንዲሰፍን ላደረጉት አስተዋጽኦ አመስግነዋል።
የሃይማኖት አባቶች ተሰሚነት ያላቸው የሰላም መልዕክተኞች በመኾናቸው ይበልጥ ሰላም እንዲመጣ ሊሠሩ እንደሚገባ ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባው ተናግረዋል።
በከተማዋ የታየው የልማት ብርሃን የሃይማኖት አባቶች ለሰላም በተወጡት ተግባር እና በመጣው አንጻራዊ ሰላም መኾኑን ያነሱት ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባው በቀጣይም ሰላምን ለማጽናት የሃይማኖት አባቶች የሚያከናውኑትን ተግባር አጠናክረው እንዲቀጥሉ ጠቁመዋል።
ዘጋቢ :- ያየህ ፈንቴ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
