
ባሕር ዳር: ኅዳር 24/2018 ዓ.ም (አሚኮ) ከፍተኛ የሥራ ኀላፊዎች በምሥራቅ ጎጃም ዞን ከብቸና ከተማ አሥተዳደር እና ከእነማይ ወረዳ ነዋሪዎች ጋር እየተወያዩ ነው።
በውይይቱ በምክትል ርእሰ መሥተዳድር ማዕረግ የአሥተዳደር ዘርፍ አሥተባባሪ አማኑኤል ፈረደ (ዶ.ር)፣ የምሥራቅ ጎጃም ዞን አሥተዳዳሪ ኑርልኝ ብርሃኑ፣ በአካባቢው የሚንቀሳቀሰው የሀገር መከላከያ ሠራዊት አዛዥ ሜጄር ጄኔራል ብርሃኑ ጥላሁን እና ሌሎች ከፍተኛ የሥራ ኀላፊዎች ተገኝተዋል።
የምሥራቅ ጎጃም ዞን አሥተዳዳሪ ኑርልኝ ብርሃኑ በክልሉ የተፈጠረው የጸጥታ ችግር ማኅበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ጉዳት አድርሷል ብለዋል። አሁን ላይ አንጻራዊ ሰላም መፈጠሩን የተናገሩት አሥተዳዳሪው ይሁን እንጅ አሁንም ቅንጅትን፣ ትብብርን የሚጠይቁ እና መፈታት ያለባቸው ችግሮች አሉ ነው ያሉት።
በማኅበራዊ እንቅስቃሴው ወደ ቀደመው አልተመለሰም፣ ነጻ የንግድ እንቅስቃሴ የለም፣ የትምህርት ሥርዓቱ ችግር ውስጥ እንደ ወደቀ ነው ብለዋል።
ለጽንፈኝነት የማይመች እና ሰላም የተረጋገጠበት አካባቢ መፍጠር እንደሚገባም ተናግረዋል። ዘረፋ እና እገታን ማስቆም እንደሚገባ ነው የተናገሩት። እውነት ላይ በመቆም፣ በመተባበር እና በአንድነት አሁን የተፈጠረውን ሰላም ዘላቂ ማድረግ ይገባናል ነው ያሉት።
ለሰላም ሲባል የሚከፈለውን ሁሉ ማድረግ እንደሚገባም ተናግረዋል። እውነት ላይ በመቆም የተፈጠረውን የጸጥታ ችግር መፍታት እና ዘላቂ ሰላምን ማረጋገጥ እንደሚገባ አመላክተዋል።
በምክትል ርእሰ መሥተዳድር ማዕረግ የአሥተዳደር ዘርፍ አሥተባባሪ አማኑኤል ፈረደ (ዶ.ር) በአማራ ክልል ተፈጥሮ የነበረው የጸጥታ ችግር በርካታ ጉዳቶችን እንዳስከተለ ተናግረዋል።
በሀገር መከላከያ ሠራዊት እና በክልሉ የጸጥታ ኃይል ተጋድሎ አሁን ላይ ክልሉ ወደ አንጻራዊ ሰላም መሸጋገሩን ገልጸዋል። ሰላምን ከማረጋገጥ ጎን ለጎን የልማት ሥራዎች እየተሠሩ መኾናቸውንም ተናግረዋል።
ሰላም ሲይዙት ቀላል፣ ሲያጡት ግን ለማግኘት በጣም ከባድ ነው ብለዋል። ባለፉት ሁለት ዓመታት በተፈጠረው የጸጥታ ችግር ልማት በአግባቡ እንዳይሄድ፤ ሕዝብም እንዲጎዳ አድርጓል ነው ያሉት።
ዜጎች በነጻነት የማይንቀሳቀሱበት ሁኔታ ተፈጥሮ መቆየቱን ተናግረዋል። ታጣቂ ቡድኖች ንጹሐንን እንደሚያግቱ እና እንደሚዘርፉም ገልጸዋል። የትምህርት ዘርፉ ሰብራት መግጠሙን የተናገሩት አሥተባባሪው በምሥራቅ ጎጃም ዞን የተፈጠረው የትምህርት ስብራት ደግሞ ከፍተኛ ነው ብለዋል። ጽንፈኛ ቡድኑ ተተኪ ትውልድ እንዳይኖር እያደረገ መኾኑንም ተናግረዋል።
በውይይት እና በምክክር ችግሮችን በመፍታት ዘላቂ ሰላምን ማረጋገጥ እና ወደ ልማት መሸጋገር ይገባል ነው ያሉት። ከዚህ ችግር በፍጥነት በመላቀቅ ወደ ተሟላ ሰላም ለመመለስ መምከር እንደሚገባም ገልጸዋል።
ማኅበረሰቡ እውነትን መሠረት በማድረግ እና ሁኔታውን በመገንዘብ መምከር እና መፍትሔ ማመላከት እንዳለበትም ተናግረዋል።
ዘጋቢ:-ታርቆ ክንዴ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
