
ባሕር ዳር: ኅዳር 24/2018 ዓ.ም (አሚኮ) እኛ ኢትዮጵያውያን “ለሰው መድኃኒቱ ሰው ነው” የሚለው ብሒል የሚገለጥብን ሕዝቦች እንደኾን ብዙውን ጊዜ በሰዎች አንደበት ይነገራል፤ ሰነድ ላይም ተከትቦ ይገኛል። ይህ በሰው ልጅ ላይ ያለ የመተማመን መንፈስን የሚያጠናክርልን የወል ነገራችን ነው።
ለአማራ ሕዝብ የባሕል መሠረተ ብዙነት ምክንያት ከኾኑ ባሕላዊ ሁኔታዎች ውስጥ የተለያዩ ባሕል እና ወግ ያላቸው ሕዝቦች ለዘመናት አብሮ የመኖር ምሥጢር ድንቅ መኾኑን የአማራ ሕዝብ ባሕል እና ቋንቋ በሚል ርዕስ የተለያዩ ምሁራን የተሳተፉበት እና በ2011 ዓ.ም የታታመው መጽሐፍ ላይ በግልጽ ሰፍሮ ይገኛል።
ክልሉ ልዩ ልዩ ሃይማኖቶች፣ ቋንቋዎች እና ባሕሎች ያሉት ለወግ እና ለማዕረጉ የሚጨነቅ ሕዝብ ያለበት ነው ሲልም ከዚሁ መጽሐፍ ላይ ተገልጿል። በዚህ ነባር ምድር ውስጥ ታዲያ ልዩ ልዩ የባሕል ቡድኖች አንዱ ሌላውን ለመጫን እና ለማጥፋት ሳይሞክር ሁሉም የየራሳቸውን ኾነው የሚኖሩበት እንደኾነም መጽሐፉ ላይ ተተንትኖ ቀርቧል።
በባሕል ድንበሩም ሳይታጠር እርስ በርስ እየተናገደ እና እየተለዋወጠ የኖረ ስለመኾኑም ያነሳል። እየተረዳዳ እና እየተደጋገፈ፣ አንድነቱ ልዩነቱን ሳይሽረው፣ ልዩነቱም አንድነቱን ሳያጠፋው ደምቀው ዘመናትን የተሻገሩ ሕዝቦች ያሉበት ነውም ይላል።
ሕዝቦቹ ችግር በገጠማቸው ዘመን ሳይቀር መደማመጥን እና መደጋገፍን መሠረት አድርገው መሻገር እንደቻሉም በመጽሐፉ ተጠቅሷል።
ይሁንና ባለፉት ሁለት እና ሦስት ዓመታት በክልሉ ከባሕል እና ከወግ ባፈነገጠ አኳዃን እንደ ሕዝብ መደማመጥ ተስኖናል ማለት ይቻላል። ባሕል እና ወጎቻችን ለችግሮቻችን መፍትሔን ማምጣት ላይም አቅም አጥተዋል ማለት ይቻላል።
ለመኾኑ አሁን ላለንበት የግጭት አዙሪት ውስጥ ልንገባ የቻልነው ምን ስለጎደለን ይኾን? የትኞቹን እሴቶቻችንስ ዘንግተን ነው ስንል ከሀገር ሽማግሌዎች እና ከሃይማኖት አባቶች ጋር ቆይታ አድርገናል።
መሪጌታ ታምር ዘላለም የሃይማኖት አባት እና የአማራ ክልል የሀገር ሽማግሌዎች መማክርት ጉባኤ ሰብሳቢ ናቸው። እንደ ሕዝብ ያጣናቸው በርካታ የትናንት መገለጫዎቻችን የነበሩ እሴቶቻችን ነው ብለዋል።
መገዳደል እና መፈላለግ የእንስሳት ባሕሪ ኾኖ ሳለ ከባሕላችን አፈንግጠን የመገዳደላችን ምሥጢሩ ባሕልን ያለመጠበቅ ዝንፈት እንደኾነ ነው የገለጹት።
ከትናንት አባቶቻችን የወረስነው ፍቅርን፣ አንድነትን፣ መከባበርን እና መደማመጥን እንደነበርም መሪጌታ ታምር ተናግረዋል። ይህ ሊያስቆጭ እና ሊያስለቅሰን የሚገባ እንደኾነም ነው የገለጹት። አሁን ላይ ትንሹ ትልቁን የማክበር እሴቱ ጥያቄ ላይ መውደቁንም አንስተዋል።
ትልቅም ትንሹን ከመውደድ ይልቅ ጠልፎ መጣልን እና በወንድም ላይ መዝመትን ልምምድ አድርገነዋል ነው ያሉት። ይህ ደግሞ የሚበላው ሁሉንም በመኾኑ ወደ ትናንት የመከባበር እና የመደማመጥ እሴቶቻችን እንመለስ ብለዋል።
ፍቅር ከፈጣሪ የተቸረ የሰው ልጆች ሁሉ ጸጋ ኾኖ ሳለ ይህን እሴት ችላ በማለታችን ዋጋ እያስከፈለን እንደኾነ ጠንቅቀን እንወቅ ነው ያሉት። አንዱ ባንዱ ላይ መጨካከን የአያት ቅድመ አያቶቻችን አይደለም ብለዋል።
ከአባቶቻችን የወረስነው ችግርን በጋራ መሻገርን እንደኾነ ነው የገለጹት። ችግር በገጠማቸው ጊዜ እንኳን አንድነትን፣ ዘዴ ማበጀትን፣ ተመካክሮ ማደርን እና ተደማምጦ መፍትሔ ማፈላለግን ነው ከአባቶቻችን የወረስነው ብለዋል።
ያም ኾኖ ይላሉ መሪጌታ ታምር አሁንም “ከገባንበት የግጭት አዙሪት መውጫ መዳኛችን መደማመጥ እና መከባበር ነው”። አሁን ላይ እንደ ክልል የተጀመረው እና እስከ ታች ድረስ እየወረደ ያለው የሀገር ሽማግሌዎች መማክርት ጉባኤ አንዱ መውጫ ዘዴ በመኾኑ ልንጠቀምበት ይገባል ሲሉም ጠቁመዋል።
“የወደቅነው መከባበር እና መደማመጥ ላይ ባሳየነው ውስንነት” በመኾኑ ባሕላዊ እሴቶቻችን ላይ እናተኩር ነው ያሉት። እርቅ እና ይቅር መባባል የማይፈታው ቀውስ አለመኖሩንም አንስተዋል።
የሃይማኖት አባቶች እና የሀገር ሽማግሌዎች በዚህ ጊዜ የመፍትሔ አካል ካልኾኑ የሕዝብ አባትነታቸው ዋጋ አይኖረውም ነው ያሉት። እምነታቸውን እና ጸጋቸውን ተጠቅመው ይህን ትውልድ ሊታደጉ እንደሚገባም ገልጸዋል።
ሌላኛው ከአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ጋር ቆይታ ያደረጉት ደግሞ የአማራ ክልል የሀገር ሽማግሌዎች መማክርት ጉባኤ ምክትል ሰብሳቢ አቶ ይመር ሰኢድ ናቸው። አሁን ላለንበት የግጭት አዙሪት የበቃነው የቀደምት አባቶቻችን እሴት ባለመጠበቃችን ነው ብለዋል። ለዚህ ትውልድ ባሕል እና ወግ ላይ ያለው የሥርጸት ማነስ ለችግር አጋልጦናል ባይ ናቸው።
እንደ ሕዝብ የቆዩ ባሕሎቻችን ከወደቁበት አንስተን ልንድንባቸው ይገባል ነው ያሉት። የመከባበር፣ የመደማመጥ፣ የመዋደድ እና ከራስ ይልቅ ለሌሎች የመኖር ባሕል ተጠቃሾች እንደኾኑም አንስተዋል።
ትውልዱ ላይ ከባሕል አንጻር ሰፊ ሥራ ይጠይቃል፤ የሀገር ሽማግሌዎች እና የሃይማኖት አባቶች ደግሞ ሰፊ ትውልድን የማሻገር ኀላፊነት አለብን ነው ያሉት። ይህን ስናደርግ መገዳደልን ሙሉ በሙሉ መቅረፍ ባንችል እንኳ መቀነስ እንችላለን ብለዋል።
የድሮ አባቶቻችን ችግር ውስጥ በወደቁ ሰዓት ረጅም ቦታ አቆራርጠው በመሄድ የተጣሉትን ያስታርቁ እንደነበርም አንስተዋል። ይህ ሲኾን የነበረው ግን ከልብ በመነጨ ፍቅር እና የመደማመጥ መንፈስ እንደነበርም ገልጸዋል። ባሕሉን ጠንቅቆ የማያውቅ ትውልድ ስለ ሰው ደንታ አይኖረውም፤ እየኾነ ያለውም ይሄው ነው ብለዋል።
አብሮ የመኖር ምሥጢሩ እርቅ እንደኾነም አቶ ይመር ገልጸዋል። መፍትሔ ይመጣ ዘንድ ነባር ባሕል ላይ መዝመት ይኖርብናል ነው ያሉት።
ያ ሲኾን መገዳደል ይቀራል፤ ወንድምም በወንድሙ ላይ አይነሳም ነው ያሉት። በአንጻሩ መደማመጥ ይነግሳል፤ ከኔ ይልቅ እኛ የሚለው አስተሳሰብ በትውልዱ ላይ ይሠርጻል ብለዋል።
ሌላኛው ያነጋገርናቸው የጎንደር ከተማ ነዋሪ እና የሀገር ሽማግሌ አቶ ሲሳይ አስማረ እንደ ሕዝብ ከደረሰብን ውጥንቅጥ እንወጣ ዘንድ ብዙ ጥረት አድርጌያለሁ ይላሉ።
ከችግራችን እንዳንወጣ ያደረገን ትናንት አባቶቻችን ያለፉበት የመደማመጥ ባሕል ባለመኖሩ ነው ባይ ናቸው።
በግጭት አዙሪት በቆየን ቁጥር ካደር አደር ለውስብስብ ችግሮች እየተዳረግን እንሄዳለን ነው ያሉት። ዋጋ የከፈልን ሕዝቦች ብንኾንም አሁንም አረፈደም የሚሉት አቶ ሲሳይ ወደ ቀደመ ባሕላችን እና ወጋችን ተመልሰን ነገሮችን በሀገር በቀል እርቅ እና ይቅርታ እንፍታ ነው ያሉት።
ዘጋቢ:- ሰለሞን አንዳርጌ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
