ለአካል ጉዳተኞች ምቹ የኾነ ተቋም በመገባት አካታችነትን ማረጋገጥ ይገባል።

9

ገንዳ ውኃ፡ ኅዳር 23/2018 ዓ.ም (አሚኮ) የምዕራብ ጎንደር ዞን ሴቶች ወጣቶች እና ማኅበራዊ ጉዳይ መምሪያ አይ ኤች ኤስ ከተባለ ግብረ ሰናይ ተቋም ጋር በመኾን በዓለም አቀፍ ደረጃ ለ34ኛ ጊዜ በሀገራችን ደግሞ ለ33ኛ ጊዜ የሚከበረውን የአካል ጉዳተኞችን ቀን በገንዳ ውኃ ከተማ አክብሯል።

ቀኑ “አካል ጉዳተኝነትን የሚያካትት ማኅበረሰብ መገባት ለተሻለ ማኅበራዊ ዕድገት” በሚል መሪ ሃሳብ ነው የተከበረው።

የምዕራብ ጎንደር ዞን ዋና አሥተዳዳሪ እያሱ ይላቅ ሰዎች አካል ጉዳተኝነትን ወደውት እና ፈቅደውት የኾኑት ሳይኾን በተፈጥሮ እና ሰው ሰራሽ አደጋዎች የሚደርስ የአካል ጉዳት ነው ብለዋል።

ለአካል ጉዳተኞች ምቹ የኾነ ተቋም በመገባት የሥራ ምቹ ኹኔታዎችን መፍጠር እና አካታችነትንም ማረጋገጥ ይገባል ነው ያሉት። የአካል ጉዳተኞችን ሁለንተናዊ ችግር የተገነዘበ ማኅበረሰብ በማፍራት አመርቂ ሥራዎችን መሥራት እንደሚገባም አስገንዝበዋል።

መንግሥትም ኾነ መንግሥታዊ ያልኾኑ ድርጅቶች አካል ጉዳተኞችን መደገፍ እና መንከባከብ እንደሚገባም ዋና አሥተዳዳሪው አስገንዝበዋል።

የምዕራብ ጎንደር ዞን የሴቶች፣ ወጣቶች እና ማኅበራዊ ጉዳይ የመምሪያ ኀላፊ ተወካይ መንግሥቱ አለማየሁ የአካል ጉዳተኞች የአካቶ ትግበራ በትኩረት መሠራት አለበት፤ ሁሉም ተቋማት ሊደግፏቸው እና አይዟችሁ ሊሏቸው ይገባል ብለዋል።

ጓዳ ውስጥ ያሉትን አካል ጉዳተኞች ወደ አደባባይ እንዲወጡ በማድረግ ሥራዎችን እንዲሠሩ እና በተለያየ ዘርፍ በኢኮኖሚ ተጠቃሚ እንዲኾኑ ሥራዎች እየተከናወኑ ስለመኾኑም ተናግረዋል።

አካል ጉዳተኞች ላይ ማኅበረሰብ የተዛባ አመለካከት ስላለው ችግሩን ለመቅረፍ የግንዛቤ ፈጠራ ሥራዎች እየተሠሩ መኾናቸውንም ገልጸዋል። የዐይነ ስውራን ስቲክ፣ ዊልቸር እና መሰል ቁሳቁሶችን ለማሟላት እየተሠራ መኾኑንም አንስተዋል።

የዞኑ የአካል ጉዳተኞች ፕሬዝዳንት መምህር ጌታ ታደሰ ማኅበሩ ከቦታ ቦታ ተንቀሳቅሶ ሥራዎችን ለመሥራት የጸጥታ ችግር እንቅፋት እንደኾነባቸው ተናግረዋል።

ማኅበሩ ቤት ለቤት ተደብቀው የተቀመጡ አካል ጉዳተኞችን በመፈለግ ትምህርት እንዲማሩ እና የተለያዩ ሥራዎችን እንዲሠሩ ጥረት እየተደረገ መኾኑን ገልጸዋል።

መብታቸውን እና ጥቅማቸውን ለማስከበር ማኅበሩ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር ሥራዎችን እየሠራ መኾኑንም ፕሬዝዳንቱ አብራርተዋል።

አካል ጉዳተኞች ከተደገፉ የመሥራት እና መሪ የመኾን አቅም እንዳላቸው ተሳታፊዎች ገልጸዋል። የሚገነቡት ሕንፃዎች፣ እና ሌሎችም መሠረተ ልማቶች አካል ጉዳተኞችን መሠረት ያደረጉ እንዲኾኑ ተሳታፊዎች ጠይቀዋል።

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleየአማራ ክልል ንግድና ገበያ ልማት ቢሮ የንግድ ሥርዓቱን የተረጋጋ ለማድረግ እየሠራ ነው።
Next articleወልድያ ጠቅላላ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል ነጻ የዓይን ሞራ ግርዶሽ ህክምና እየሰጠ ነው።