የአማራ ክልል ንግድና ገበያ ልማት ቢሮ የንግድ ሥርዓቱን የተረጋጋ ለማድረግ እየሠራ ነው።

6

ባሕር ዳር: ኅዳር 23/2018 ዓ.ም (አሚኮ) የአማራ ክልል ንግድና ገበያ ልማት ቢሮ የንግድ መሰረትን ማስፋት፣ ሕገወጥ የንግድ ሥርዓት፣ የኑሮ ውድነት ማሻሻል እና የኤክስፖርት ምርትን በተመለከተ የአራት ወራት ዕቅድ አፈፃፀም ላይ መግለጫ ሰጥተዋል።

የአማራ ክልል ንግድና ገበያ ልማት ቢሮ ኅላፊ ኢብራሒም ሙሐመድ (ዶ.ር) ደግሞ መግለጫውን ሰጥተዋል።

ንግድን ዘመናዊ፣ ተወዳዳሪ፣ ተደራሽ እና ፍትሐዊ ለማድረግ የንግድ እና የግብይት ሥርዓቱን ለማዘመን በቴክኖሎጂ መደገፍ አለበት ብለዋል።

ከነበረው ኋላቀር አሠራር በመውጣት የነዳጅ ሽያጭ፣ የንግድ ፈቃድ እና እድሳት፣ የገበያ ዋጋ መረጃ እና የምርት ትስስር ሂደትን በቴክኖሎጂ ለማገዝ እየተሠራ መኾኑን ተናግረዋል።

ያለመሰረተ ልማት ንግድና ገበያ ልማት ሊሳካ አይችልም ያሉት ኀላፊው ንግድና ገበያ ልማትን በቴክኖሎጂ እያዘመንን ነው ብለዋል።

60 ሺህ 550 ነጋዴዎች በአዲስ የንግድ ሥርዓቱን ተቀላቅለዋል፤ ይህም ከእቅዳችን አኳያ ከእቅድ በላይ ነው ብለዋል።

በፀጥታ ችግር በዋናነት የሚጎዳው የንግድ ሥርዓቱን ነው ያሉት ኀላፊው እንደ ክልል 352 ሺህ ነጋዴዎች መኖራቸውን ጠቅሰዋል። ከእነዚህ ውስጥ 278 ሺህ ነጋዴዎች ቁጥጥር መደረጉን አንስተዋል።

ቁጥጥር ከተደረገባቸው 278 ሺህ የንግድ ድርጅቶች ውስጥ 39 ሺህ የሚኾኑት ከቀላል እስከ ከባድ ስህተት ተስተውሎባቸዋል ብለዋል።

117 ሺህ ሊትር ነዳጅ በሕገወጥ መንገድ ሲዘዋወር መያዙንም ዶክተር ኢብራሂም አብራርተዋል።

ሕገወጥ ኬላ የመንግሥትም፣ የሕዝብም ፍላጎት አይደለም ያሉት ዶክተር ኢብራሂም በሸማቾች እና በነጋዴዎችም ላይ ትልቅ ችግር እየፈጠረ ነው ብለዋል።

በሀገር ደረጃ ብሎም እንደ ክልል ውይይት ተካሂዶ ኬላ ሕገወጥ ነው የሚል አቆም ተወስዷል ነው ያሉት።

ዘጋቢ:- ሰመሀል ፍስሀ

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን

Previous article“የችግር መፍቻው ግጭት እና ጦርነት መኾን የለበትም” ርእሰ መሥተዳድር አረጋ ከበደ
Next articleለአካል ጉዳተኞች ምቹ የኾነ ተቋም በመገባት አካታችነትን ማረጋገጥ ይገባል።