ከባሕር ዳር እስከ ተረሳው ቤተ መንግሥት።

512

ባሕር ዳር፡ ሰኔ 13/2012 ዓ.ም (አብመድ) ወርኃ መጋቢት በገባ በመጀመሪያው ቀን ነበር። ባሕር ዳር ከተማ በሙቀትና በተሽከርካሪ ብዛት ደምቃለች። የፀሐይ ወበቅ ቃታ ይነሳል፤ እኩለ ቀን ደርሷል። ወይ ምድር ስንቱን ቻለችው፣ ከላይ ሙቀቱ ከስር ክፋቱ እና ምቀኝነቱ አንገብግቧተል። እንደምድር የተሰቃዬ ማን አለ? ፈጣሪ ከምድር የበለጠ ታጋሽ የፈጠረ አይመስለኝም። ለምን ቢሉ የተለያዬ ፅንፍ የረገጡ ሐሳቦችንና ተግባሮችን አቅፋ ይዛለችና ነው። የፀሐይ ብርሃን እየተጋረፈ ባለበት ሰዓት በባሕር ዳር ምዕራባዊ አቅጣጫ ወጥተን ወደ ባሕር ዳር አውሮፕላን ማረፊያ አመራን።

ውቢቷ ባሕር ዳርን ለማዬት ወደ ስፍራው የሚመጣ ሁሉ ከአውሮፕላን ማረፊያው ጀምሮ ከተማ እስኪገባ ድረስ ያለውን መንገድ ሲያይ በአዕምሮው ስሏት የመጣችው ከተማ ትኮሰምንበታለች። ከአውሮፕላን ማረፊያው ጀምሮ በተለምዶ ገጠር መንገድ እስኪባለው ሰፈር ድረስ ያለው መንገድ አስቸጋሪ በመሆኑ ነው ጎብኚውን ግራ የሚያጋበው። በቀጭኑ በተነጠፈችው አስፓልት መረጋጋት የማያውቁ የሞተር ብስክሌት ጋላቢዎች፣ ጋሬዎች፣ ታክሲዎች እና ከአየር መንገድ እንግዳ የሚቀበሉ ልዩ ልዩ መኪኖች መንገዷን ያጨናንቋታል። መንገዷ ሰው ከተሽከርካሪ ጋር እየተጋፋ የሚያልፍባት ናት። መንገዱን ለማስፋት የተጀመረው ሥራም የኤሊ ጉዞ ላይ ነው። ጎብኚው ይህን መንገድ ሲያይ የባሕር ዳር ውበት ላይ ጥያቄ ቢፈጥርበትም መንገዱን እንደጨረሰ ግን በአዕምሮው የሳላት በልቡ የተመኛት ውቢቷ ባሕር ዳርን ያገኛል።

ከመንገዶቹ ዳር ለዳር ደግሞ መንግሥት ቆጥሮ ያልተረከባቸውና እንዲሠሩ ያልፈቀደላቸው ሕገ ወጥ ግንባታዎች የከተማዋ የውበት እድፎች ሆነዋል። በእርግጥ እነርሱም ማደሪያ አጥተው እንጂ በሕገወጥ መንገድ የመሥራት አባዜ ኖሮባቸው አይመስለኝም። በሕጋዊ መንገድ ለተደራጁት ቦታ አለመስጠት አንደኛው ለሕገወጥ ቤት ግንባታ አባባሽ ምክንያት ነው። በነገራችን ላይ ከሦስት ዓመት በፊት ከዘመድም፣ ከአብቁተም ተበድረው በሕጋዊ መንገድ ቦታ ለማግኘት የሚጠበቅባቸውን ቁጠባ ያሟሉ ግን እስከዛሬ በከተማ አስተዳደሩ ቁራጭ ቦታ የተነፈጋቸው ሕጋዊ በመቶዎች የሚቆጠሩ ማኅበራት አሉ፡፡ በአንጻሩ በሺዎች የሚቆጠሩ ሕገ ወጥ ገንቢዎች ቢያንስ ለጊዜው እየኖሩበት ነው፡፡

የባሕር ዳር አውሮፕላንን ማረፊያ ሊዳረሱ ሲሉ በቀኝ በኩል ወደ ወገርሳና ቁንዝላ የሚወስድ የጠጠር መንገድ ይገኛል። እርሱን መንገድ ይዘን የባሕር ዳር አውሮፕላን ማረፊያን ወደግራ በመተው ጉዟችን ቀጠልን። የኢትዮጵያ መካላከያ ሠራዊት የምዕራብ ዕዝ መቀመጫ የነበረ የአየር ኃይል መንደር ከዘመኑ ጋር መጓዝ ተስኖት ባለበት እንደቆመ ይታያል። በደርግ ዘመነ መንግሥት እንደተሠሩ የሚነገርላቸው ቤቶች የእርጅና ቀንበር ተጭኗቸዋል። በቤቶቹ አለመታደስ ያላሰብኩት ቁጭት ተሰማኝ። ሕይወቱን ገብሮ ከእንቅልፍ እና ከምቾት ዓለም ተሰናብቶ ያልተደፈረች ኢትዮጵያን ለሚጠብቀው ጀግና ወታደር እውን ያ ቤት ይገበዋልን? ስል ራሴን ጠየኩ፤ በእውነቱ አይገባውም! ‘‘ለነገሩ ወታደር ወጥቶ የሚያድር፣ ውሎ ማደሪያው ዱርና ገደል የሆነ ለሰው የሚኖር ከሞት ጋር ወዳጅነት የፈጠረ ስለሆነ ቤቱ ላያስፈልገው ይችላል’’ ስልም እራሴን አፅናናሁ። ቤቶቹ ከዘመኑ ጋር መራመድ ቢያቅታቸውም በቤቶቹ ዙሪያ ከዘመኑ ጋር የሚራመዱ ጀግና ወታደሮችና የጦር መሳሪያዎች እንዳሉ ስላሰብኩ ደስ አለኝ።

መልካሙ ምድር በረከት አልተለየውም፤ ጠራራ ፀሐይ በተመላበት የመጋቢት ወር እንኳን ልምላሜ እንደለበሰ ነው። ማሳው በውበት እንደተጎናፀፈም ነው። ጉዟችን በጣና ራስጌ ነው። ጣና ፀሐይ በበረታበት እኩለ ቀን ሲታይ ሰማይን የነካ ይመስላል። ደመና የማይታይበት የጠራው ሰማይ ጣና ላይ የተነከረ መስሏል። ሰማዩን ሽቅብ ሲመለከቱት የእንባ ዘለላ የሚመስል ነገር ይታይበታል። አንዳችም የደመና ብናኝ ዓይታይም። ከጣና ባሻገር የምድር ጫፍ ይመስላል። አይ ጣና? ለኢትዮጵያውያን የተሰጠ መና ሆኖ ሳለ ከመናው ቆርሶ የበላ ግን የለም። ጣና የኢትዮጵያውያን የታሪክ መሸፈኛ የወርቅ ጌጥም ነው። ወደ ቀኝ ትተነው ጉዟችን ቀጠለ።

በእርግጥ ጣና አካባቢውን ይዞረዋል፤ ወይም አካባቢው ጣናን ይዞረዋል። ትንሽ የገጠር መንደሮችን እያቆራረጥን ወደፊት ገሰገስን። በሥራ ላይ ያለው የጠጠር መንገድ አቧራ በመንገዱ ዳር ያሉ ቤቶችን በቁፋሮ የተገኙ አስመስሏቸዋል። ‘‘ከተመኙ ላይቀር ወንዝን ነው መመኜት ከአገር ሳይለቁ ሰው አገር መገኜት’’ እንዳለ ከያኒው መነሻውን ከጎጃም ምድር አድርጎ ሜድትራኒያን ባሕር ድረስ የተዘረጋውን የግዮን ወንዝን አገኜን። ታላቁ ግዮን መነሻው ከኤዶም ገነት ምንጭ ሆኖ ገነትን ከሚያጠጡ አራት አፍላጋት አንዱ እንደሆነና የኢትዮጵያን ምድር እንደሚከብ መጽሐፍ ቅዱስ ይናገራል።

እኛ ስሙን ቀይረን ‘ዓባይ’ አልነው፤ ግብጾች ‘ናይል’ አሉት፤ ታላቁ ግዮን እኛ ‘አባይ፣ ውሸታም፣ ከሀዲ’ ያልነው፤ ግብጾች ደግሞ ‘ናልኝ፤ እፈልግሃለሁ’ አሉት መስሎት የበረሃ ተጓዥ ሆኖ ቁልቁል ይነጉዳል፤ እኛን ያራቁታል፤ ግብጽን የበረሃ ገነት ያደርጋል፡፡ ከሰከላ ተራሮች ተነስቶ በምዕራብ በኩል ጣናን የሚያገኘው ዓባይ በጣና ታዝሎ ሐይቁን ይሻገራል፤ ጣናም ቃሉን አክባሪ እርግት ስክን ያለ ለእምነቱ ያደረ ነውና ከውኃው ውኃ ቀላቅሎ አያስቀርም፡፡

ዓባይን ተሻገርን፣ በአጠገቡ የሚያታዩትን ለምለም ስፍራዎች ቃኝተን ወደፊት ጉዟችንን ቀጥለናል። ‘‘የፊተኞች ኋለኞች፤ ኋለኞችም ፊተኞች ይሆናሉ’’ ይሉት ብሂል የደረሰባት የደረሰባት ቀደምት ከተማ አገኘን። ዘመኑ ረስቷታል፤ ከቆዘመችበት የድብርት ድባብ አልነቃችም። ዕድሜ ጠገብ ቤቶቿ ለመፍረስ ተቃርበዋል። ከጉያዋ የምታመነጨው ብርሃን ለእርሷ ጥለውን ጥሎ አሻግሮ ያበራል፤ የወለዱት ሳይባረክ ሲቀር እንደቁንዝላ ነው። ቁንዝላ ወደብ በመሆን ታገለግል እንደ ነበር ይነገርላታል። ታዲያ በዚያ ዘመን የዘመነችው ቁንዝላ ዛሬም በዚያ ዘመን ላይ እንደተቀመጠች ትገኛለች። ኃይል ታመነጫለች፤ ኃይል ግን አታገኝም፤ ‘ሞኝ አሳላፊ ዘመዱን ይጎዳል’ ነገር ሆኖባታል፡፡ ታዝቦ ከማለፍ የዘለለ አማራጭ አልነበረንም፤ በትዝበት አልፈናት ወደፊት ገሰገስን። ትንንሽ መንደሮችን እና ደንገል በርን አልፈን ወደፊት ከነፍን።

ከላይ ከታች የሚያነጥረው መንገድ አቅል ይነሳል። ከባሕር ዳር 80 ኪሎ ሜትር ገደማ ተጉዘናል። ጀንበር ጉልበቷ እየደከመ መጥቷል፤ ወደ ምዕራብ መስኮቷም ማዘቅዘቅ ጀምራለች። ተናፋቂ ባሕሪዋን ለማምጣት ተዘጋጅታለች። ‘‘አለፋ ጣቁሳ ሞፈር መቁረጥ ያውቃል፣ ካልተለበለበ መቼ ይታረቃል’’ እውነትም ሞፈር መቁረጥ ያውቃል። በመልካም ሞፈር የታረሰው ማሳ መልካም ዘር ይዞ እንደከረመ ቃርሚያው ይናገራል። አለፋጣቁሳ ቀደም ባለው ጊዜ በአንድ ወረዳ ስር ሲተዳደር የነበረ ትርፍ አምራች ከሚባሉ የጎንደር አካባቢዎች አንዱ ነው። አሁን ላይ ግን አለፋ እና ጣቁሳ ተብሎ በሁለት ወረዳ ተከፍሏል። የመጀመሪያው ቀን መዳረሻችን አለፋ ነበርና ከወረዳው ሻውራ ከተማ ጀንበርን በስስት እያዬን ሸኘናት።

ሻውራ ረዘም ያለ ዓመታትን ያስቆጠረች እንደሆነች ይነገርላታል። ለከተማዋ ረጅም ዕድሜ ማሳለፍ ምስክር የምትሆነው ደግሞ በ14ኛው መቶ ክፍለ ዘመን እንደተሠራች የሚነገርላት የማርያም ቤተክርስቲያን ናት። ከተማዋም በዚህ ዘመን እንደተቆረቆረች ነው የሚነገረው። አለፋ ትርፍ አምራች፣ ቋራን ባቋራጭ የሚያገናኝ ሆኖ ሳለ ዛሬ ድረስ ባልሰላ መንገድ መቆየቱ ግርምትን የሚፈጥር ነው። እኩለ ቀን ገደማ የተጀመረው ጉዟችን ሻውራ ላይ ቢጠናቀቅም አንድ መልካም ነገር ለማዬት ቸኩያለሁ። ልቤ ወደ ከጀለው ስፍራ ከሚወስደን ባለሙያ ጋር ተገናተን በጠዋት ወደስፍራው ለማቅናት ቀጠሮ ያዝን። ከቀኑ የተረፈችን ጥቂት ሰዓት ከተማዋን እና እንቅስቃሴዋን በማዬት አሳልፈን ነው ጀንበርን በናፍቆት የሸኘናት። ከተማዋ የመብራት ችግር እንዳለባት ነዋሪዎቹን መጠየቅ አያሻም።

ከጀንበር ጋር ወደ መኝታ ክፍሌ ገባሁ፤ በደቂቃዎች ውስጥ በእንቅልፍ ሰመመን ተወሰድኩ፤ ደክሞኛላ! ወዲያው የማያቋርጥ የሚንደቀደቅ ድምጽ ይሰማኝ ጀመረ፤ አልጋዬ ላይ እየተገላበጥኩ ድምጹን እሰማለሁ፡፡ በመከላከያ ሄሊኮፕተር እየበረርኩ ወይም ሄሊኮፕተሯ እየዞረችኝ ይመስለኛል፡፡ ድምጹ አይርቅም፤ አይቀርብም፡፡ ጓደኛ መጥቶ የመኝታ ቤቱን በር አንኳኳ፤ ብንን ብዬ ተነሳሁ፤ በሕልሜ ይመስኝ የነበረው ድምጽ አልተቋረጠም፤ ለካስ የኤሌክትሪክ ኃይል ስለሌለ በጀኔሬተር ስለሚጠቀሙ ነው፡፡ እራት ለመብላት ከጓደኞቼ ጋር ወደ ከተማዋ መካከል ተንቀሳቀስን፤ የጀኔሬተሮች ድምጽ ከተማዋን ሲንጣት አቅል ያስታል፤ እንደምንም ራት በልተን ከድምጹ ለመገላገል እየናፈቀን ወደ መኝታ ክፍላችን ገባን፤ እስከ ምሽት 4፡00 በድምጽ ስትናጥ ያመሸቸው ከተማ ድንገት ፀጥ እረጭ አለች፤ ሕይወት በሻውራ ምሽት እንዲህ ናት፤ የኤሌክትሪክ አገልግሎት ቢኖርም ብዙ ቀን የለም፤ የኃይል መቆራረጡ የበዛ ስለሆነ በየቤቱ ጀኔሬተር አለ፡፡ ተኝቻለሁ፤ ከጠዋት ጀምሮ ደግሞ ቀጠሮ ወደያዝንለት ቦታ እንሄዳለን!

ይቀጥላል …

ዘጋቢ፡- ታርቆ ክንዴ

ተጨማሪ መረጃዎችን
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
ትዊተር https://bit.ly/37m6a4m
ዩቱዩብ https://bit.ly/38mpvDC ያገኛሉ፡፡

Previous articleአመልድ ለ256 ሺህ በላይ ቤተሰቦች ድጋፍ እያደረገ ነው፡፡
Next articleበኩር ጋዜጣ ሰኔ 15-2012 ዓ/ም