
ባሕር ዳር: ኅዳር 23/2018 ዓ.ም (አሚኮ) ርእሰ መሥተዳድር አረጋ ከበደ ከደብረ ማርቆስ ከተማ
አሥተዳደር ነዋሪዎች ጋር በወቅታዊ ጉዳዮች ላይ ተወያይተዋል።
በውይይቱ ከርእሰ መሥተዳድር አረጋ ከበደ በተጨማሪ ምክትል ርእሰ መሥተዳድር አብዱ ሁሴን (ዶ.ር)፣ በምክትል ርእሰ መሥተዳድር ማዕረግ የአሥተዳደር ዘርፍ አሥተባባሪ አማኑኤል ፈረደ (ዶ.ር) እና ሌሎች ከፍተኛ የሥራ ኀላፊዎች ተገኝተዋል።
የአማራ ክልል ርእሰ መሥተዳድር አረጋ ከበደ ሰላምን ለማረጋገጥ ችግሩ ላይ መግባባት ያስፈልጋል ብለዋል። ሁልጊዜም ቢኾን “የችግር መፍቻው ግጭት እና ጦርነት መኾን የለበትም” ነው ያሉት። ግጭትን እንደ ችግር መፍቻ አድርጎ መጠቀም እንደማይገባም ተናግረዋል።
የአማራ ሕዝብ መሠረታዊ ጥያቄዎች በጦርነት እንደማይፈቱም ገልጸዋል። ችግሮች የሚፈቱት በውይይት እና በምክክር ነው ብለዋል። መንግሥት ጥያቄዎችን ቆጥሮ ይዞ ለመፍታት እየሠራ መኾኑንም አስታውቀዋል።
የዓለም ልምድ ችግሮችን በውይይት መፍታት ነው ያሉት ርእሰ መሥተዳድሩ የኢትዮጵያ መንግሥትም ችግሮችን በውይይት ለመፍታት ጽኑ ፍላጎት አለው ነው ያሉት። ለዚህም ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ተቋቁሞ እየተሠራ መኾኑን ተናግረዋል። የአማራ ክልል ሕዝብም ለሀገራዊ ምክክር ኮሚሽኑ አጀንዳዎች ማሰባሰቡን ተናግረዋል።
መንግሥት ተደጋጋሚ የሰላም እና የውይይት ጥሪ አቅርቧል ያሉት ርእሰ መሥተዳድሩ የግጭት መጨረሻው ውይይት ነው ብለዋል። መንግሥት ሁልጊዜም ለውይይት በሩ ክፍት መኾኑንም ተናግረዋል። ነገር ግን የውይይት ሃሳቦችን የማይቀበሉ ታጣቂዎች መኖራቸውን ነው የገለጹት።
መንግሥት ሰላምን ለማረጋገጥ የመጀመሪያው አማራጭ ብሎ የያዘው የሰላም አማራጭን ነው፤ ይህን በማይቀበሉ ላይ ግን ሕግ መከበር ስላለበት ሕግ እናስከብራለን ብለዋል። በአማራ ክልል የሚንቀሳቀሰው ኃይል በሕዝብ ላይ በርካታ ችግሮችን አድርሷል ነው ያሉት። የሃይማኖት አባቶች ታጣቂዎችን መምከር፣ መገሰጽ እና ለሰላም መሥራት እንደሚገባቸውም ርእሰ መሥተዳድሩ አሳስበዋል።
የከተማዋ መሪዎች ሕገ ወጥ ንግድን፣ የአገልግሎት አሰጣጥ ችግርን መፍታት እንደሚጠበቅባቸውም አሳስበዋል።
ለሀገር ሰላም እና ክብር እየሠራ የሚገኘውን የሀገር መከላከያ ሠራዊት ስም ማጠልሸት እንደማይገባም አስገንዝበዋል። በሀሰተኛ መረጃ ጦርነቱ እንዲባባስ የሚሠሩትን ማውገዝ እንደሚጠበቅም ገልጸዋል።
በክልሉ የተፈጠረው የጸጥታ ችግር ተማሪዎችን ከትምህርት ገበታ በማራቅ፣ ንብረት በማውደም እና ሰብዓዊ ኪሳራ እንዲደርስ በማድረግ ክልሉን ጎዳ እንጂ ጥቅም የለውም ነው ያሉት።
እንደ ሀገር የሚጠቅሙ መልካም እሳቤዎችን እና ሥራዎችን ማጉላት፣ የሚለያዩትን ደግሞ መተው ይጠበቃል ብለዋል። ውሸትን ከእውነት ለይቶ መረዳት እና ማስረዳት ይገባል፤ ሀገርን እየጎዳ ያለው ሀሰተኛ ፕሮፖጋንዳ ነው፣ አካባቢያችሁን ነቅታችሁ ጠብቁ ነው ያሉት።
በከተማዋ የተነሱ የልማት እና የመልካም አሥተዳደር ጥያቄዎችን ለመፍታት እንደሚሠራም አመላክተዋል።
ዘጋቢ:-ታርቆ ክንዴ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
