“ሚናን ለይቶ ለመፍትሔ መቆም ሰላምን ያረጋግጣል” ምክትል ርእሰ መሥተዳድር አብዱ ሁሴን (ዶ.ር)

8

ባሕር ዳር: ኅዳር 23/2018 ዓ.ም (አሚኮ) የአማራ ክልል ከፍተኛ መሪዎች ከደብረ ማርቆስ ከተማ ነዋሪዎች ጋር በወቅታዊ ጉዳዮች ላይ ተወያይተዋል።

በውይይቱ ርእሰ መሥተዳድር አረጋ ከበደ፣ ምክትል ርእሰ መሥተዳድር አብዱ ሁሴን (ዶ.ር)፣ በምክትል ርእሰ መሥተዳድር ማዕረግ የአሥተዳደር ዘርፍ አሥተባባሪ አማኑኤል ፈረደ (ዶ.ር) እና ሌሎች ከፍተኛ የሥራ ኀላፊዎች ተገኝተዋል።

የሀገር መከላከያ ሠራዊት ከፍተኛ አመራሩ ሜጄር ጄኔራል ብርሃኑ ጥላሁን ችግሮቻችንን ለመፍታት መወያየት ተጠናክሮ መቀጠል አለበት ብለዋል። የሀገር መከለካያ ሠራዊት የሕዝብን ሰላም ለማረጋገጥ እየሠራ መኾኑንም ተናግረዋል።

ሠራዊቱ የዜጎችን ሰብዓዊ እና ዴሞክራሲያዊ መብቶችን ለማስከበር የሚሠራ መኾኑንም ገልጸዋል። ሠራዊቱ ከሀገሩ አልፎ በጎረቤት ሀገራት ሰላም የሚያስከብር የኢትዮጵያ ኩራት እና ክብር መኾኑንም ተናግረዋል።

ሠራዊቱን በአልተገባ ፕሮፖጋንዳ ስሙን ማጠልሸት ተገቢ አለመኾኑንም አስገንዝበዋል። በሕዝብ ላይ ግፍ የሚፈጽሙ ቡድኖችን ማውገዝ እና መታገል እንደሚገባም አሳስበዋል። ሠራዊቱ የሚወጣ እና የሚወርደው ለሀገር ሰላም ብሎ እንጂ ለማንም ብሎ አይደለም ነው ያሉት።

በኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት ልክ ለሕዝብ ሲል ጫካ ለጫካ የሚንከራተት የለም ብለዋል። ለሀገር ሰላም የምንሠራው እኛ፣ ከኢትዮጵያ ጠላቶች ጋር የምንዋጋው እኛ ኾነን ሳለ እኛን ባልተገባ መንገድ መውቀስ እና መክሰስ ልክ አይደለም ነው ያሉት።

በሀሰተኛ ፕሮፖጋንዳ እና በተሳሳተ አቅጣጫ ሰላምን ማረጋገጥ እንደማይቻል የተናገሩት አዛዡ እውነት ላይ ቆማችሁ ንጹሐንን የሚበድሉትን አውግዙ ብለዋል።

የሀገር መከለካያ ሠራዊት ሕግ ለማስከበር ነው የቆመው፤ ሕግ ለማስከበር በሚደረገው ሂደት ውስጥ የራሳችሁን ጥረት ማድረግ አለባችሁ ነው ያሉት።

የአማራ ክልል ምክትል ርእሰ መሥተዳድር አብዱ ሁሴን (ዶ.ር) ሕዝብ ለሰላም መካሪ እና ዘካሪ እንዲኾን የችግሩ መነሻ ምን እንደኾነ ማወቅ እና ማሳወቅ ይገባል ነው ያሉት። የአማራ ሕዝብ ጥያቄዎችን ለማስመለስ ግጭት እና ጦርነት ሳይኾን ውይይት እና ምክክር ነው የሚያስፈልገው ብለዋል።

የልማት እና የመልካም አሥተዳደር ጥያቄዎችን ለመፍታት እየተሠራ ነው፤ ነገር ግን በሂደት እንጂ በአንድ ጀንበር አይፈታም፤ ይሄን ማወቅ ይገባል ብለዋል።

የመልካም አሥተዳደር፣ የኑሮ ውድነትን፣ የሥራ አጥነትን እና ሌሎች ችግሮችን ለመፍታት ሰላምን ማረጋገጥ እንደሚገባም ተናግረዋል። መሪዎችን በግፍ የሚገድሉትን፣ ንጹሐንን የሚያሰቃዩትን በድፍረት ማውገዝ ካልቻላችሁ ሰላምን ማረጋገጥ አይቻልም ነው ያሉት።

ከአስተዋይ ሕዝብ የሚጠበቀው ሐቅን መረዳት እና ክፉውን ማውገዝ ነው ብለዋል። ክፉ የሚያደርጉትን፣ እና ግፍ የሚፈጽሙትን ማውገዝ ይገባል ነው ያሉት።

ታጣቂ ኃይል የአማራ ሕዝብ ጥያቄዎችን ያራዝም ይኾናል እንጂ ማስፈታት አይችልም ነው ያሉት። “ሚናን ለይቶ ለመፍትሔ መቆም ሰላምን ያረጋግጣል” ብለዋል። ቢቻል ሚናን ለይቶ ችግርን መፍታት እንጅ ችግርን ማወሳሰብ አይገባም ነው ያሉት።

እርስ በእርስ በመነጋገር እና በመደራጀት የአካባቢያቸውን ሰላም እንዲጠብቁም አሳስበዋል።

ዘጋቢ:-ታርቆ ክንዴ

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleግጭት አክሳሪ እንጂ አትራፊ አይደለም።
Next article“የችግር መፍቻው ግጭት እና ጦርነት መኾን የለበትም” ርእሰ መሥተዳድር አረጋ ከበደ