ግጭት አክሳሪ እንጂ አትራፊ አይደለም።

6

ባሕር ዳር: ኅዳር 23/2018 ዓ.ም (አሚኮ) ርእሰ መሥተዳድር አረጋ ከበደ ከደብረ ማርቆስ ከተማ አሥተዳደር ነዋሪዎች ጋር ተወያይተዋል።

በውይይቱ ከርእሰ መሥተዳድር አረጋ ከበደ በተጨማሪ ምክትል ርእሰ መሥተዳድር አብዱ ሁሴን (ዶ.ር)፣ በምክትል ርእሰ መሥተዳድር ማዕረግ የአሥተዳደር ዘርፍ አሥተባባሪ አማኑኤል ፈረደ (ዶ.ር) እና ሌሎች ከፍተኛ የሥራ ኀላፊዎች ተገኝተዋል።

የውይይቱ ተሳታፊዎች በክልሉ በተፈጠረው የጸጥታ ችግር ምክንያት ለከፋ ችግር ተዳርገን ቆይተናል ብለዋል። አሁን ላይ ያለውን አንጻራዊ ሰላም ወደ ዘላቂ ሰላም ማሸጋገር እንደሚገባም ተናግረዋል።

የደብረ ማርቆስ – አዲስ አበባን መንገድ ደኅንነት ማረጋገጥ እንደሚገባም ገልጸዋል። የጸጥታ ችግሩ የኑሮ ውድነትን እያባባሰ እና ነዋሪዎችን በእጅጉ እየጎዳ መኾኑንም ተናግረዋል። ተማሪዎች ከትምህርት ገበታ ውጭ ኾነው መክረማቸውንም አንስተዋል። በዚህ ከቀጠለ ነገ ከነገ ወዲያ የተማረ ትውልድ አይኖርም ነው ያሉት።

ችግሮችን በውይይት እና በንግግር በመፍታት ለሕዝብ እረፍት መስጠት እንደሚገባ ተናግረዋል። ለግጭት አባባሽ የኾኑ መልካም አሥተዳደርን፣ ሌብነትን፣ የአገልግሎት አሰጣጥ ችግሮችን መፍታት እንደሚገባ ገልጸዋል። የመንግሥት ተቋማት አገልግሎት አሰጣጣቸውን እንዲያስተካክሉም ጠይቀዋል።

እርሰ በእርስ ካለመተማመን በመውጣት ችግሮችን መፍታት እና ዘላቂ ሰላምን መፍታት ይገባል ነው ያሉት። በሃይማኖት ተቋማት እና በመንግሥት ተቋማት ሕዝብን ለመነጠል የሚሠሩ ሥራዎችን ማስተካከል እንደሚገባ አንስተዋል። በክልሉ ያለው “ግጭት አክሳሪ እንጂ አትራፊ አይደለም”፤ በተለይም በገጠር አካባቢ ሕዝቡ በየቀኑ አምጣ እየተባለ እየተሰቃየ ነው፤ እየታገተ ገንዘብ እየተጠየቀ ነው ብለዋል። መታገትን እና ዘረፋን ማስቆም እንደሚገባም ተናግረዋል።

ሰላምን በማረጋገጥ ወደ ናፈቀን ልማት መመለስ አለብን ነው ያሉት። ከተማዋ በግጭት ምክንያት በታሪኳ ልክ መልማት እና ማደግ አለመቻሏንም ተናግረዋል።

በግጭት ምክንያት ባለሃብቶች ወደ ተሟላ ሥራ እንዳይገቡ እና አካባቢውን ለቀው እንዲወጡ ኾኗል ነው ያሉት። በጦርነት እና በግጭት የሚመለስ የሕዝብ ሰላም፣ የሚረጋገጥ ሰላም የለም ብለዋል። ወጣቶች የሃይማኖት አባቶችን እና የሀገር ሽማግሌዎችን ምክር እና ተግሳጽ መስማት እንደሚገባቸውም አንስተዋል።

ሰላም የምናመጣው እኛው ነን፣ ከማንም አይመጣም፣ ከቤተሰቦቻችን ጀምረን ስለ ሰላም እንሥራ፣ ክፉውን ነገር እንተውው፣ ያን ጊዜ ሰላም ይመጣል ነው ያሉት። ሰላምን ማረጋገጥ የሚቻለው መመካከር፣ መረዳዳት እና በአንድነት መቆም ስንችል ነው ብለዋል።

የደብረ ማርቆስ ከተማ አሥተዳደር ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ ተሾመ ዋለ ከተማዋ ጸጋ እያላት ነገር ግን በጸጋዋ ልክ መልማት ሳትችል የቆየች መኾኗን ገልጸዋል። በከተማዋ የሚነሱ የልማት እና የመልካም አሥተዳደር ችግሮችን ለመፍታት እንደሚሠሩም ተናግረዋል።

በአንድነት እና በትብብር መሥራት ከቻልን ከተማዋን ማልማት እና ተወዳዳሪ ማድረግ እንችላለን ነው ያሉት። አለመደማመጥ ለችግር ዳርጎን ቆይቷል ያሉት ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባው በመደማመጥ እና የራሳችንን ድርሻ በመውሰድ ችግሮችን በራሳችን አቅም መፍታት አለብን ብለዋል።

የሃይማኖት አባቶች፣ የሀገር ሽማግሌዎች፣ ወጣቶች እና ሌሎች የማኅበረሰብ ክፍሎች የድርሻቸውን እንዲወጡም አስገንዝበዋል። እውነትን መረዳት፣ እውነት ላይ ቆሞ ለሰላም መሥራት እንደሚገባ ተናግረዋል። ክፉ የሚያደርጉትን መገሰጽ እንደሚጠበቅም ገልጸዋል። መመካከር እና መግባባት ከቻልን ችግር መፍታት የሚያስችል አቅም አለን ነው ያሉት።

ሰላማችን ማረጋገጥ ከቻልን በአጭር ጊዜ ውስጥ መለወጥ የሚችል የልማት አቅም አለ ብለዋል። ከሕዝብ እና ከመሪዎች ጋር ተግባብቶ ከተሠራ በአጭር ጊዜ ውስጥ ለውጥ ማምጣት እንደሚቻልም አንስተዋል።

ዘጋቢ:-ታርቆ ክንዴ

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous article“በትብብር በመሥራት ሀገራዊ የፍትሕ ሥርዓቱን ማላቅ ይገባል” የአማራ ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዝዳንት ዓለምአንተ አግደው
Next article“ሚናን ለይቶ ለመፍትሔ መቆም ሰላምን ያረጋግጣል” ምክትል ርእሰ መሥተዳድር አብዱ ሁሴን (ዶ.ር)