
ባሕር ዳር: ኅዳር 23/2018 ዓ.ም (አሚኮ) የሐረሪ ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት መሪዎች በባሕር ዳር ከተማ ተገኝተው የአማራ ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት የለውጥ ሥራዎችን እየጎበኙ ነው።
የሐረሪ ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዝዳንት ሳለሐዲን ተውፊቅ፣ ምክትል ፕሬዝዳንት አሻ አሚኔ እና ሌሎችም የሥራ ኀላፊዎች ናቸው ጉብኝት ያደረጉት።
የጉብኝቱ ዋና አላማ በጠቅላይ ፍርድ ቤቶች መካከል ያለውን ቅንጅታዊ አሠራር በማጠናከር የለውጥ ሥራዎችን ውጤታማ ለማድረግ እና ጥራት ያለው የፍትሕ ሥርዓት ለመዘርጋት በማሰብ ነው።
የአማራ ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዝዳንት ዓለምአንተ አግደው እንግዶችን ተቀብለው ሥለተቋሙ የለውጥ ሥራዎች እና የሥራ እንቅስቃሴ ገለጻ አድርገዋል።
የአማራ ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት በጠንካራ መሪዎች ታግዞ የለውጥ ሥራዎችን በፍጥነት በማከናዎን ፍትሕን በጥራት እና በቅልጥፍና ተደራሽ ለማድረግ እየሠራ ያለ ተቋም ስለመኾኑም አንስተዋል።
ዜጎች በየትኛውም ቦታ ጥራት ያለው አገልግሎት እንዲያገኙ እንደ ሀገር በጋራ እየተሠራ ነው፤ ከቦታ ቦታ የሚለያየውን የአፈጻጸም ልዩነት በማጥበብ ወጥ እና ተገማች አገልግሎት መስጠት ያስፈልጋል ብለዋል።
ፍትሕ በተወሰነ አካባቢ ብቻ ሳይኾን በሁሉም የሀገሪቱ አካባቢዎች መረጋገጥ አለበት፤ የአማራ ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት በዘርፉ እያከናወናቸው ያሉ የለውጥ ሥራዎችን ለሀረሪ ክልል አቻ ተቋም በተሞክሮነት ያካፍላል፤ ከሀረሪ ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤትም የሚወሰዱትን ተሞክሮዎች እንጋራለን ነው ያሉት።
“በትብብር በመሥራት ሀገራዊ የፍትሕ ሥርዓቱን ማላቅ ይገባል” ሲሉም አስገንዝበዋል። መላው የክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤቶች ለጋራ ራዕይ ተቀራርበው እና በትብብር መሥራት እንደሚጠበቅባቸውም አቶ ዓለምአንተ መልዕክት አስተላልፈዋል።
የሐረሪ ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዝዳንት ሳለሐዲን ተውፊቅ እንደ ሀገር በሁሉም ክልሎች የፍትሕ ማሻሻያ ሥርዓት እየተተገበረ ስለመኾኑ ጠቅሰው የአማራ ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት በአዲስ አመራር ተዋቅሮ አርዓያ የሚኾኑ፣ ፈጣን እና ውጤታማ የለውጥ ሥራዎችን እንዳከናወነ ገልጸዋል።
በመኾኑም ከዚሁ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ልምድ እና ተሞክሮዎችን ለመውሰድ ወደ ባሕር ዳር መምጣታቸውን ተናግረዋል።
የአማራ ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት እውነትም በቴክኖሎጅ የላቀ፣ ምቹ የሥራ ቦታን የፈጠረ እና የአመራር ቁርጠኝነትን ያረጋገጠ ስለመኾኑም በምልከታቸው ስለማረጋገጣቸውም ተናግረዋል።
የተመለከቱት ስኬታማ ለውጥ የሐረሪ ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት እያደረገ ላለው ዘርፈ ብዙ የማሻሻያ ሥራዎችን ተሞክሮዎችን እንዲወስድ ያስችላል ብለዋል ፕሬዝዳንቱ።
ከፌዴራል እና ከክልሎች ጠቅላይ ፍርድ ቤቶች ጋር ያለውን ቅንጅታዊ አሠራር እና ትብብር በማጠናከር እንደ ሀገር ወጥ የኾነ ፍትሕ ተደራሽ ማድረግ እንደሚገባም አንስተዋል።
በልምድ ልውውጡ ላይ የተገኙት የሀረሪ ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት የዳኞች አሥተዳደር ጉባኤ ጽሕፈት ቤት ኀላፊ ፈርሐን መሐመድ የአማራ ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ሀገራዊ የፍትሕ ማሻሻያ ሥራውን አፍጥኖ እና አልቆ መፈጸሙን ተመልክተናል ብለዋል። የተመለከቱትን አሠራር ወደ ተቋማቸው ወስደው በመተግበር ለሀገርም የሚበጅ ዘመናዊ እና ጠንካራ የፍትሕ ሥርዓት ለመገንባት እንደሚሠሩም ተናግረዋል።
የሁሉም ክልሎች ጠቅላይ ፍርድ ቤቶች በጋራ በመሥራት እና ያሏቸውን ልምዶች እና አሠራሮች በመቀመር ሀገራዊ የፍትሕ ሥርዓቱን ማላቅ እንደሚገባም ገልጸዋል።
በተወሰኑ አካባቢዎች ብቻ የሚተገበር ፍትሕ የሀገርን የፍትሕ ሥርዓት ሙሉ ሊያደርግ እንደማይችልም አንስተዋል።
ዘጋቢ፦ አሚናዳብ አራጋው
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
