
ባሕር ዳር: ኅዳር 23/2018 ዓ.ም (አሚኮ) የአማራ ክልል ሴቶች፣ ወጣቶች እና ማኅበራዊ ጉዳይ ቢሮ “አካል ጉዳተኝነትን የሚያካትት ማኅበረሰብ መገንባት ለተሻለ ማኅበራዊ እድገት” በሚል መሪ መልዕክት የአካል ጉዳተኞች መብት መከበር እና ሁለንተናዊ ተሳትፎ ለማሳደግ በሚያስችሉ ጉዳዮች ዙሪያ ከክልል ተቋማት ጋር እየመከረ ነው።
በመርሐ ግብሩ መልዕክት ያስተላለፉት በምክትል ርእሠ መሥተዳድር ማዕረግ የማኅበራዊ ዘርፍ አሥተባባሪ ሙሉነሽ ደሴ (ዶ.ር) የአካል ጉዳተኞች ቀን አንድ ጊዜ ብቻ የሚከበር ሳይኾን ዓመቱን ሙሉ የሚታሰብ ጉዳይ ነው ብለዋል።
የአካል ጉዳተኝነት ፈተናዎች ከባሕል፣ ከአስተሳሰብ፣ ከመሠረተ ልማት እና ከሌሎችም በርካታ ምክንያቶች የሚመነጩ ዘርፈ ብዙ ችግሮች ናቸው ብለዋል። እነዚህን ፈተናዎችን ለመቋቋም ከአስተሳሰብ መጀመር እንደሚገባ ተናግረዋል።
የአካል ጉዳተኝነት እና ፈተናዎቻቸው በታዳጊ ሀገራት በአሳሳቢ ደረጃ ላይ እንደሚገኝ አመላክተዋል። በሀገራችንም በየጊዜው እያጋጠሙ ባሉት ግጭቶች እና ጦርነቶች ምክንያት የአካል ጉዳተኞች ቁጥር እየጨመረ መምጣቱን ጠቁመዋል።
ከቁጥራቸው አንጻር ሁለንተናዊ ተጠቃሚነታቸው በሚፈለገው ልክ አለመኾኑን ገልጸዋል። ይህንን በመገንዘብ ሁሉም አካላት ትኩረት መሥጠት ይገባቸዋል ነው ያሉት። አካል ጉዳተኞችን በሁሉም የልማት ዘርፎች ማሳተፍ እና መደገፍ እንደሚገባ አሳስበዋል።
የአማራ ክልል ሴቶች፣ ወጣቶች እና ማኅበራዊ ጉዳይ ቢሮ ኀላፊ ብርቱካን ሲሳይ አካል ጉዳተኞች በማኅበራዊ፣ በፖለቲካዊ እና ኢኮኖሚያዊ ጉዳዮች ተጠቃሚነታቸው እንዲረጋገጥ በቢሮው በኩል ሰፊ ሥራዎች እየተሠሩ መኾኑን ተናግረዋል።
በዚህ ዓመትም የአካል ጉዳተኞች ቀንን መሠረት በማድረግ የግንዛቤ ፈጠራ ሥራዎች ሲሠሩ መቆየታቸውን ገልጸዋል።
በየተቋማቱ የአካል ጉዳተኞች በሚፈለገው መንገድ አካትቶ መሥራትን በተመለከተ ክትትል እየተደረገ ስለመኾኑም ጠቁመዋል። አካል ጉዳተኞች ባለ ምጡቅ አዕምሮ መኾናቸውን በመገንዘብ ማካተት እና ትኩረት ሰጥቶ ማሳተፍ እንደሚገባ ገልጸዋል።
አካል ጉዳተኞች ድጋፍ እና እንክብካቤ ይፈልጋሉ ያሉት ቢሮ ኀላፊዋ የመንግሥት፣ የግል እና የሲቪል ተቋማትም ምቹ ሁኔታን መፍጠር እንደሚገባቸው አመላክተዋል።
በእቅዶቻቸው እና በማንኛውም መርሐ ግብሮቻቸው በማካተት አካል ጉዳተኞች ከራሳቸው አልፎ ለሀገር ልማት የበኩላቸውን አስተዋጽኦ እንዲያበረክቱ ማስቻል ከተቋማት እንደሚጠበቅ አስገንዝበዋል።
ዘጋቢ:- አሰፋ ልጥገበው
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን
