‎የእርሻ ሥራን እስከ ምርት ስብሰባ ድረስ ዘመናዊ መሣሪያዎችን በመጠቀም ማዘመን ያስፈልጋል።

3

ባሕር ዳር: ኅዳር 23/2018 ዓ.ም (አሚኮ) ‎የሰሜን ጎጃም ዞን ግብርና መምሪያ “ጉዞ ወደ ሜካናይዜሽን” በሚል እሳቤ የግብርና ሜካናይዜሽን የንቅናቄ መድረክን እያካሄደ ነው፡፡

‎በመድረኩ ከሁሉም ወረዳዎች የመጡ ከፍተኛ የሥራ ኀላፊዎች፣ ሞዴል አርሶ አደሮች እና የኅብረት ሥራ ዩኒዬኖች ተገኝተዋል።

‎የሰሜን ጎጃም ዞን ምክትል አሥተዳዳሪ እና የግብርና መምሪያ ኀላፊ በለጠ ጥጋቡ የሰሜን ጎጃም ዞን እምቅ የግብርና አቅም ያለው እና ከ315 ሺህ ሄክታር በላይ በመኸር የሚታረስ መሬት ያለበት ዞን ነው ብለዋል።

‎ለብዙ ሺህ ዓመታት በበሬ ሲታረስ ኖሯል፤ ይህም በግብርናው እድገት ላይ ተጽዕኖ አሳድሮበታል ነው ያሉት። የግብርና ሥራው ከእርሻ እስከ ጉርሻ ድረስ በበሬ ጫንቃ የተንጠለጠለ ኾኖ ቆይቷል ነው ያሉት።

‎በዚህ ዘመን ታሪኩን በመቀየር የእርሻ ሥራ እስከ ምርት ስብሰባው ድረስ ዘመናዊ መሣሪያዎችን በመጠቀም ግብርናን ማዘመን እንደሚያስፈልግ ገልጸዋል።

‎መዋቅራዊ ሽግግር የማይቀር ነው ያሉት ምክትል አሥተዳዳሪው ግብርናው አምርቶ ለኢንዱስትሪው ያስረክባል ብለዋል። ስለዚህ ግብርናው ካልዘመነ መዋቅራዊ ሽግግር አይሳካም ነው ያሉት።

‎‎በዞኑ 100 ትራክተሮችን እና 50 ኮምባይነር ለማሠራጨት በዕቅድ የተያዘ ቢኾንም እስካሁን ከፍላጎት ባለፈ የተሠራ ሥራ አለመኖሩን ተናግረዋል።

‎የመድረኩ አስፈላጊነትም ፈጻሚው፣ አርሶ አደሮች እና ኅብረት ሥራ ማኅበራት በጋራ ኾነው ሜካናይዝድ የኾኑ የግብርና መሣሪያዎችን ለአርሶ አደሮች እንዲያቀርቡ ለማስቻል እና እንዲጠቀሙ ለማድረግ ነው ብለዋል።

‎የመድረኩ ተሳታፊዎች በወረዳ ቢያንስ ሦስት ትራክተር እንዲገዛ ማድረግ ተገቢ እንደኾነ አንስተዋል።

‎እንደ ዞን ሰብል በኮምባይነር የሚሰበሰብ ቢኾንም ኮምባይነሮቹ ከሌላ ክልል የሚመጡ በመኾናቸው እና በዞኑ ያለውን አቅም ተጠቅሞ ማሽኖችን ማቅረብ አስፈላጊ መኾኑንም ገልጸዋል።

‎ዘጋቢ፦ ፍሬሕይዎት አዘዘው

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleበኦሮሞ ብሔረሰብ አሥተዳደር እየተሠሩ ያሉ የልማት ሥራዎች በሚኒስትሮች እየተጎበኙ ነው።
Next articleኢሠማኮ የኢትዮጵያ ሠራተኞች ድምፅ በአፍሪካም ኾነ በዓለም አደባባይ እንዲሰማ እየሠራ ነው።