አመልድ ለ256 ሺህ በላይ ቤተሰቦች ድጋፍ እያደረገ ነው፡፡

503

ባሕር ዳር፡ ሰኔ 13/2012 ዓ.ም (አብመድ) የአማራ መልሶ መቋቋምና ልማት ድርጅት (አመልድ) የኮሮናቫይረስን ለመከላከል ከ43 ሚሊዮን ብር በላይ መድቦ እየሠራ መሆኑን አስታውቋል፡፡

የአመልድ የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ እሱባለው ድረስ ለአብመድ እንደገለጹት አመልድ በክልሉ ዘርፈ ብዙ የልማት ሥራዎችን እያከናወነ ነው፡፡ የአካባቢና ደን ልማት፣ የተሻለ የግብርና ስልት እንዲፈጠር፣ የመስኖ ልማት፣ የንጹሕ መጠጥ ውኃ እና የወጣቶች የሥራ ዕድል ፈጠራ ላይ እንደሚሠራ ተናግረዋል፡፡

በዚህ ወቅት ሕዝብን ለማዳን በሚደረገው ጥረት አመልድ የበኩሉን ድርሻ እየተወጣ መሆኑንም ኃላፊው ተናግረዋል፡፡ ድርጅቱ ፕሮጀክቶቹን በሚተገብርባቸው በሁሉም አካባቢዎች 43 ሚሊዮን 37 ሺህ 633 ብር በመበጀት የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ ቅድመ መከላከል ሥራ እየሠራ መሆኑን ገልጸዋል፡፡ አመልድ በክልሉ የእንቅስቃሴ ገደብ በጣለበት ወቅት ድጋፍ ለሚሹ ወገኖች የሁለት ሚሊዮን ብር የምግብ ድጋፍ ማድረጉንም ኃላፊው እሱባለው ድረስ አስታውሰዋል፡፡

ወረርሽኙ እየተስፋፋ ሲመጣ አደጋውን ለመቀነስ የሚያስችሉ ስልቶችን ነድፎ እየተንቀሳቀሰ መሆኑንም አቶ እሱባለው ድረስ አስታውቀዋል፡፡ ድርጅቱ የልማት ፕሮጀክቶቹ በሚተገበሩባቸው አካባቢዎች ለዜጎች የንጽሕና መጠበቂያ ሳኒታይዘር፣ አልኮል፣ ጭንብል ድጋፍ እያደረገ መሆኑንም አስረድተዋል፡፡ የውኃ ማጠራቀሚያ ችግር ላለባቸው አካባቢዎች 10 ሺህ ሊትር የሚይዙ የውኃ ፓንፖችን በመሠራጨት ላይ መሆናቸውም ታውቋል፡፡

በአመልድ ‘አራተኛው ልማታዊ የምግብ ዋስትና ፕሮግራም ተቋማት አይበገሬነትን ማጠናከር ፕሮጀክት’ ከአሜሪካ ሕዝብና መንግሥት በተገኘ 86 ነጥብ 6 ሚሊዮን የአሜሪካን ዶላር የገንዘብ ድጋፍ ከኬር ኢትዮጵያ እና ወርልድ ቪዥን ጋር በመተባበር ለምግብ ዋስትና ተጋላጭ የሆኑ 256 ሺህ 329 ነዋሪዎችን ኑሮ ለማሻሻል እየሠራ መሆኑንም አስታውቀዋል፡፡ ድጋፉ የሚደረግባቸው 207 ቀበሌዎችን የሚያዳርስ ነውም ብለዋል፡፡

ድርጅቱ ከልማት ሥራዎቹ ጎን ለጎን ድጋፉን አጠናክሮ እንደሚቀጥል ኃላፊው ተናግረዋል፡፡

ዘጋቢ፡- ታርቆ ክንዴ

ተጨማሪ መረጃዎችን
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
ትዊተር https://bit.ly/37m6a4m
ዩቱዩብ https://bit.ly/38mpvDC ያገኛሉ፡፡

Previous articleየጤና አገልግሎት ግንዛቤ ፈጠራ ሥራዎች ውጤት ሊያመጡ በሚችል መልኩ ተጠናክረው መቀጠል እንዳለባቸው ቋሚ ኮሚቴው አሳሰበ፡፡
Next articleከባሕር ዳር እስከ ተረሳው ቤተ መንግሥት።