
ደብረ ማርቆስ: ኅዳር 22/2018 ዓ.ም (አሚኮ) የምሥራቅ ጎጃም ዞን “ተግዳሮቶችን በመቋቋም የኤች አይ ቪ ኤድስ ምላሽን በዘላቂነት እናረጋግጣለን” በሚል መሪ መልዕክት የኤድስ ቀን ባለድርሻ አካላት በተገኙበት አክብሯል።
የምሥራቅ ጎጃም ዞን ጤና መምሪያ የዓለም የኤች አይ ቪ ኤድስ ቀንን ሲያከብር ተሳታፊ ኾነው ያገኘናቸው ወይዘሮ ባዩሽ አጥናፉ ከ1998 ዓ.ም ጀምሮ የኤች አይ ቪ ቫይረስ በደማቸው መኖሩን አውቀው በቤዛ በጎ አድራጎት ማኅበር ውስጥ በመቀላቀል የበሽታውን ሥርጭት ለመቀነስ “ትውልድ ይዳን በእኛ ይብቃ” በማለት በማስተማር ላይ እንደሚገኙ ነግረውናል።
በማኅበረሰቡ ዘንድ በአሁኑ ወቅት ከፍተኛ መዘናጋት ይስተዋላል ያሉት ወይዘሮ ባዩሽ የሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ግንዛቤ ፈጠራ ላይ ትኩረት ሰጥተው ሊሠሩ እንደሚገባ ነው የገለጹት።
ሲቪኤም እና ናፓድ ከተባሉ መንግሥታዊ ካልኾኑ ድርጅቶች የመጡ ባለድርሻ አካላትም የኤች አይቪ ኤድስ ቫይረስ ሥርጭትን ለመከላከል አፍላ ወጣቶች ላይ ትኩረት አድርገው እየሠሩ መኾኑን ተናግረዋል።
በምስራቅ ጎጃም ዞን የኤች አይቪ ኤድስ ሥርጭት በአሁኑ ወቅት እየጨመረ መምጣቱን የተናገሩት የዞኑ የኤች አይ ቪ ኤድስ መከላከል እና መቆጣጠር ዘርፈ ብዙ ምላሽ ቡድን መሪ አፈወርቅ ሰለሞን ቫይረሱ የተገኘባቸው የማኅበረሰብ ክፍሎች የመድኃኒት ተጠቃሚ እንዲኾኑ እየተደረገ ነው ብለዋል።
የምስራቅ ጎጃም ዞን ጤና መምሪያ ተወካይ ኀላፊ ጌታነህ ጋሻው በዞኑ የኤች አይቪ ኤድስ ሥርጭትን ለመከላከል ከግንዛቤ ፈጠራ ጀምሮ የሕክምና አገልግሎቱን ተደራሽ በማድረግ ተጋላጭ የማኅበረሰብ ክፍሎች ላይ ትኩረት ተሰጥቶ ይሠራል ነው ያሉት። ከባለድርሻ አካላት ጋር በመቀናጀትም የኤች አይ ቪ ኤድስ በሽታውን ለመከላከል እንደሚሠራም ተናግረዋል።
የኤች አይ ቪ ኤድስ ቀን በዓለም አቀፍ ደረጃ ለ38ኛ ጊዜ፣ በኢትዮጵያ ደግሞ ለ37ኛ ጊዜ ነው እየተከበረ ያለው።
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
