አካል ጉዳተኞች እንደማንኛውም ሰው ዕድል ይፈልጋሉ።

12
ባሕር ዳር: ኅዳር 22/2018 ዓ.ም (አሚኮ) “አካል ጉዳተኞችን የሚያካትት ማኅበረሰብ መገንባት ለተሻለ ማኅበራዊ እድገት” በሚል መሪ መልዕክት በዓለም አቀፍ ደረጃ ለ34ኛ ጊዜ በሀገራችን ደግሞ ለ33ኛ ጊዜ የአካል ጉዳተኞች ቀን ይከበራል።
የአማራ ክልል ሴቶች፣ ወጣቶች እና ማኅበራዊ ጉዳይ ቢሮ ከአማራ ክልል አካል ጉዳተኞች ፌዴሬሽን ጋር በጋራ በመኾን ቀኑን አስመልክቶ መግለጫ ሰጥተዋል።
የአማራ ክልል ሴቶች፣ ወጣቶች እና ማኅበራዊ ጉዳይ ቢሮ ኀላፊ ብርቱካን ሢሣይ አካል ጉዳተኞችን በማኅበራዊ፣ በፖለቲካዊ እና በኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴ ውስጥ ፍትሐዊ ተሳታፊ እና ተጠቃሚ እንዲኾኑ ማድረግ ይገባል ብለዋል ።
የአካል ጉዳተኞች ቀን በመንግሥት፣ በሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅት እና በንግድ ተጠቃሚ እና ተሳታፊ እንዲኾኑ ዘርፈ ብዙ ሥራዎች የሚሠራበት መድረክ እንደኾነ ነው የገለጹት።
በአካል ጉዳተኞች ዙሪያ የወጡ ፖሊሲዎች፣ አዋጆች እና መመሪያዎች ለራሳቸው ለአካል ጉዳተኞች እና ለማኅበረሰቡ ሰፊ የግንዛቤ ማስጨበጫ የሚፈጠርበት እንደኾነም ተናግረዋል።
የአካል ጉዳተኞች ቀን መከበር አቅም ለሌላቸው አካል ጉዳተኞች ሀብት በማሰባሰብ ድጋፍ የምናደርግበት፤ መሥራት የሚችሉ አካል ጉዳተኞችን ደግሞ ወደ ሥራ የምናስገባበት፤ ውጤታማ የኾኑ አካል ጉዳተኞችን እውቅና የምንሰጥበት እና ሌሎች አካል ጉዳተኞች እንዲነቃቁ ዕድል ለመፍጠር ሰፊ ሥራ የምንሠራበት መንገድ ነውም ብለዋል።
እንደ ክልል 361 የሚኾኑ የአካል ጉዳተኞች ማኅበራት አሉ ያሉት ኀላፊዋ ማኅበራቱን ሰብስቦ በአንድ የያዘ 91 የአካል ጉዳተኞች ፌዴሬሽን መኖሩንም ነው የገለጹት።
ፌዴሬሽኑ ለማኅበራቱ ድጋፍ እና ክትትል በማድረግ ጠንካራ እንዲኾኑ ይሠራልም ብለዋል። መብታቸውን እና የኢኮኖሚ ተጠቃሚነታቸውን እንዲያረጋግጡ በማድረግ የተለያዩ ሥልጠናወችን በማዘጋጀት እንዲበቁም ይደረጋል ነው ያሉት።
አካል ጉዳተኞች መሥራት ይችላሉ፤ “አካል ጉዳተኞች እንደማንኛውም ሰው ዕድል ነው የሚያስፈልጋቸው”፤ ምቹ ኹኔታ ከተመቻቸላቸው የመሥራት፣ የመለወጥ፣ ሃሳብን የማፍለቅ፣ በያዙት ነገር ላይ ውጤታማ የመኾን ትልቅ ችሎታ አላቸው ብለዋል።
አካል ጉዳተኞች ሀገራቸውን እና ራሳቸውን የሚጠቅም ሥራ እንዲሠሩ ማድረግ የሁላችንም ርብርብ ይጠይቃል ነው ያሉት ኅላፊዋ።
የአማራ ክልል አካል ጉዳተኞች ማኅበራት ፌዴሬሽን ፕሬዝዳንት ፍሬሰላም ዘገየ የአካል ጉዳተኞች ፌዴሬሽን ዋና ሥራው ለአካል ጉዳተኞች ድምጽ ኾኖ በአካል ጉዳተኞች እና በመንግሥት መካከል እንደ ድልድይ ማገልገል ነው ብለዋል።
በሁሉም አካባቢዎች ኅዳር ወርን ለአካል ጉዳተኞች በመሰየም ሁሉም ቦታዎች ላይ ንቅናቄ በመፍጠር በርከት ያሉ ተግባራትን እየሠራን እንገኛለን ነው ያሉት።
ከግንዛቤ ፈጠራ አኳያ ከማኅበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ተሀድሶ ጋር በተያያዘ ሥራዎችን በከተማም፣ በወረዳም፣ በዞንም ደረጃ እየተሠራ ነው ብለዋል።
በኢኮኖሚ ተሀድሶ ከ3 ሺህ በላይ ለሚኾኑ አካል ጉዳተኞች በቋሚነት እና በግዜያዊነት የምግብ፣ የአልባሳት እና ሌሎችም ድጋፎች ይደረጋሉ ሲል ፍሬሰላም ዘገየ ተናግረዋል ።
ቀኑ ሲከበር ከማኅበራዊ ተሀድሶ አንጻር የጤና አገልግሎትን ማመቻቸት፣ የትምህርት አገልግሎትን ማመቻቸት እና ለአካል ጉዳተኞች ምቹ እና ተደራሽ ማድረግ የንቅናቄው ዋና ተግባር ይኾናል ብለዋል ።
ዘጋቢ:- ሰመሀል ፍስሀ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
Previous article‎ጤናማ ዜጋ መፍጠር ለዘላቂ ሰላም እና ልማት ወሳኝ ነው፡፡
Next articleበኩር ጋዜጣ ኅዳር 15/2018 ዓ.ም