‎ጤናማ ዜጋ መፍጠር ለዘላቂ ሰላም እና ልማት ወሳኝ ነው፡፡

10
ባሕር ዳር: ኅዳር 22/2018 ዓ.ም (አሚኮ) ‎የአማራ ክልል ጤና ቢሮ ዓለም አቀፍ የኤድስ ቀንን አስመልክቶ በባሕር ዳር ከተማ የፓናል ውይይት መድረክ አካሂዷል፡፡
‎በዓሉ በየዓመቱ ኅዳር 22 የሚከበር ሲኾን ዛሬም ”ተግዳሮቶችን በመቋቋም የኤች አይ ቪ ኤድስ ምላሽን በዘላቂነት እናረጋግጥ” በሚል መሪ መልዕክት በዓለም አቀፍ ደረጃ ለ38ኛ ጊዜ፣ በሀገር አቀፍ ደረጃ ደግሞ ለ37ኛ ጊዜ ተከብሯል፡፡
‎በመድረኩ ስለበሽታው ግንዛቤ የሚያስጨብጥ በዓሉን መሰረት ያደረገ መነሻ ጽሑፍ ቀርቦ ውይይት ተካሂዷል፡፡
‎የኤች አይ ቪ ኤድስ ከፍተኛ ችግር ያደርስበት የነበረውን ከባዱን ጊዜ ሥራዎችን በመሥራት ለውጥ መምጣቱ፣ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ደግሞ በሽታውን ለመከላከል የሚደረገው ጥረት መቀዛቀዙን፣ የጸጥታ ችግር መኖሩም ለችግሩ አስተዋጽኦ እንዳለው በተሳታፊዎች ተጠቅሷል፡፡
‎በሽታው የልማት እንቅፋት በመኾኑ በንቃት የመከላከል ሥራው ላይ መሠራት እንዳለበት እና ለዚህም የሚመለከታቸው አካላት የድርሻቸውን መወጣት እንዳለባቸው ሀሳቦችን አንስተዋል፡፡ በየተቋማት ያሉ መልካም ተሞክሮዎች፣ ችግሮች እና ጥያቄዎች ተነስተው ከመድረክ ምላሽ ተሰጥቶባቸዋል፡፡
‎የአማራ ክልል ጤና ቢሮ ኀላፊ አብዱልከሪም መንግሥቱ ኤች አይ ቪ ኤድስ ጤናማ፣ አምራች፣ ደኅንነቱ የተጠበቀ እና የበለጸገ ማኅበረሰብ የመፍጠር ትልቅ ራዕይ ሊያሰናክል የሚችል በሽታ መኾኑን አንስተዋል፡፡ በሽታውን ለመከላከል በሚከናወኑ የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥራዎች የባሕርይ ለውጥ ሥርጸት ላይ መሻሻል መኖሩን እና አሁንም ልዩ ርብርብ እንደሚጠይቅ መረጃዎች ያሳያሉ ብለዋል፡፡
‎የበሽታው ምርመራ እና የሕክምና አገልግሎቶች በየደረጃው በጤና ተቋማት እየተሠጠ ነው፤ በውጤቱም ሥርጭቱን መቀነስ ተችሏል ብለዋል፡፡ በሽታው ወጣቶችን እና ሴቶችን ይበልጥ የሚያጠቃ በመኾኑ አጋላጭ ሁኔታዎች ላይ መሠረታዊ ለውጥ ለማምጣት መሠራት እንዳለበት ተናግረዋል፡፡
‎ከ3 ሺህ 600 በላይ ሰዎች በየዓመቱ በበሽታው እንደሚሞቱ ይገመታል ያሉት ኀላፊው ለተጋላጭ የኅብረተሰብ ክፍሎችን በጥልቅ የባሕሪ ተግባቦት ሥርጸት ሥራዎች እየተሠሩ ነው ብለዋል፡፡ በሽታውን ለመከላከል እና ለመቆጣጠር ሁሉም የማኅበረሰብ ክፍል በቅንጅት መሥራት እንዳለበት ተናግረዋል፡፡
‎በምክትል ርእሰ መሥተዳደር ማዕረግ የማኅበራዊ ዘርፍ አሥተባባሪ ሙሉነሽ ደሴ (ዶ.ር) የኤድስ ቀን በየዓመቱ መከበሩ በሽታውን ለመከላከል እና ስለበሽታው ግንዛቤ ለማስጨበጥ ያስችላል ብለዋል።
‎‌የበዓሉ መከበር ዋና ዓላማው የችግሩን ስፋት እና ግዝፈት ለባለድርሻ አካላት እንዲደርስ ለማድረግ፣ በበሽታው ላይ የተፈጠረውን መዘናጋት እና የሚያስከትለውን ችግር ለማስረዳት ያግዛል ነው ያሉት። የመንግሥት መሪዎች ትልቅ ኀላፊነት ያለባቸው መኾኑን አውቀው እንዲሠሩ ታሳቢ ያደረገ ነውም ብለዋል።
‎‌የበዓሉ መከበር በሽታው የዓለም የጋራ ጠላት መኾኑን ተረድቶ ለመከላከል የጋራ ግንዛቤ እንዲኖር ማድረግ እና አሠራር መፍጠር የሚጠበቁ ውጤቶች ናቸው ብለዋል። ‎‌የኤችአይቪ/ኤድስ ሕክምና እና አገልግሎቱን ለሁሉም ያለአድሎ ማዳረስ፣ እየቀጠለ ያለውን ሕመም እና ሞት መከላከል እና ማስቆም ያስፈልጋል ነው ያሉት።
‎‌የኤችአይቪ/ኤድስ ሥርጭት በሀገር ደረጃ 0 ነጥብ 5 በመቶ ሲኾን በክልል ደረጃ ደግሞ 1 ነጥብ 1 በመቶ ነው። እንደ ሀገር በየዓመቱ በበሽታው የሚያዙ ሰዎች ቁጥር 7 ሺህ 962 ሲኾን በክልሉ ደግሞ 3 ሺህ 414 መኾኑን አንስተዋል። ይህም አብዛኛው ቁጥር በአማራ ክልል መኾኑን ያመላክታል ነው ያሉት፡፡
‎የሥርጭት መጠኑ በተለይ በሕጻናት እና ሴቶች ላይ ከፍተኛ ነው፤ በሚሞቱ ሰዎች ምክንያትም ሕጻናት ያለአሳዳጊ እና አረጋውያን ያለ ጧሪ እየቀሩ ነው ብለዋል፡፡
‎በሽታውን መከላከል እና መኖር እየተቻለ የሚሞተው በዝቷል ያሉት አስተባባሪዋ በተለይም በከተሞች ላይ ያለው ሥርጭት ከፍተኛ መኾኑን ተናግረዋል፡፡
‎የኤችአይቪ/ኤድስ በደማቸው ከሚገኙት መካከል 61 በመቶ የሚኾኑት ሴቶች ናቸው፤ ይህ ደግሞ ችግሩን ያባብሰዋል ነው ያሉት፡፡
‎የበሽታው አጋላጭ ሁኔታዎች ላይ በመሥራት፣ ስለበሽታው ያለውን ነባራዊ ሁኔታ ግንዛቤ በመያዝ በሽታውን መከላከል ላይ ትኩረት ተደርጎ መሠራት እንዳለበት አሳስበዋል፡፡ በሽታው የሚያስከትለውን አደጋ በልኩ በመረዳት በሽታውን መከላከል ይገባል በማለት ጤናማ ዜጋ መፍጠር ለዘላቂ ሰላም እና ልማት ወሳኝ ነው ሲሉ መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል፡፡
‎ዘጋቢ:- ፍሬሕይወት አዘዘው
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
Previous article“አሚኮ ለሀገር እድገት የሚበጅ የመገናኛ ብዙኀን አገልግሎት እየሰጠ የሚገኝ ጠንካራ ተቋም ነው” ሚኒስትር ዴኤታ ስለሽ ግርማ
Next articleአካል ጉዳተኞች እንደማንኛውም ሰው ዕድል ይፈልጋሉ።